ማራቶንን በክብረ ወሰን በማሸነፍ ታሪክ እያስመዘገበች ያለችው ትዕግሥት አሰፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሴቶች ማራቶን ውድድር ላይ ከፍተኛውን የሰዓት ቅናሽ በማምጣት ባለፈው ዓመት ክብረወሰን የሰበረችው ትዕግሥት አሰፋ በኦሊምፒክ መድረክ ባይሳካላትም በታላቁ የለንደን ማራቶን አሸናፊ በመሆን ክብረ ወሰን አስመዝግባላች።
ኢትዮጵያዊቷ ትዕግሥት በለንደን ማራቶን አሸናፊ በመሆን ድል የተቀዳጀችው ሴቶች ብቻ በተሳተፉበት የማራቶን ውድድርን ክብረወሰንን ለግማሽ ደቂቃ በቀረበ ጊዜ ለማሻሻል ችላለች።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ከኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ ተፎካክራ ትዕግሥት ሁለተኛ በመሆን የኦሊምፒክ ብር ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።
ትዕግሥት አሰፋ በእሁዱ የለንደን ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ውድድሩን ከአራት ዓመት በፊት ያሸነፈችውን ኬንያዊቷን ጆይስሊን ጄፕኮስጌይን አስር ኪሎሜትር እየቀራት በሰፊ ልዩነት ርቃት በመሄድ ነው። ውድድሩን ስታጠናቅቅም ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ የሆነ ጊዜን አስመዝግባለች።
በትዕግሥት አሰፋ የተቀደሙት ኬንያዊቷ ጄፕኮስጌይን ሦስት ደቂቃ ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ሁለተኛ ስትወጣ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ደግሞ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቃለች።
አሁን ትዕግሥት ያስመዘገበችው ሰዓት ባለፈው ዓመት በተደረገው የለንደን ማራቶን በኬንያዊቷ ፔሬዝ ጄፕቺርቺር ተይዞ የነበረውን የውድድሩን ክብረ ወሰን በ26 ሰከንዶች ለማሻሻል አስችሏታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትዕግሥት አሰፋ ባለፈው ዓመት መስከረም 13/2016 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን በተካሄደው 48ኛው የበርሊን ማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ መግባቷ ይታወሳል።
ውዝግብ ተሰምቶበት ከነበረው የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር በኋላ የዓለማችን ሴት የማራቶን ኃያላን የሆኑት ትዕግሥት አሰፋ እና ሲፋን ሐሰን የተሳተፉበት ይህ የዘንድሮው የለንደን ማራቶን ከባድ ፉክክር የሚደረግበት ነው ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
በፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ላይ ትዕግሥት እና ሲፋን እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ እግር በእግር እየተከታተሉ በመሮጥ አስደናቂ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን፣ በመጨረሻ ላይ ሁለቱ አትሌቶች መካከል በተፈጠረው አካላዊ ንክኪ ምክንያት ትዕግስት በሲፋን ተገፍታ ሚዛኗን በመሳቷ ሲፈን አሸናፊ ሆናለች የሚል ውዝግብ ተነስቶ ነበር።
ቢሆንም ግን ቅሬታው ተቀባይነት ሳያገኝ ሲፋን የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር አሸናፊ በመሆን ክብሩን ወስዳለች። ትዕግሥትም ጠብር ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ይህ ክስተትም ሁለቱ አትሌቶች በቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች ላይ የበላይ በመሆን የፓሪስ ኦሊምፒክ ውዝግብን መቋጫ ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቆይቷል።
ስለዚህም የለንደን ማራቶን ውድድር በአዘጋጆቹ እና በአትሌትክስ አፍቃሪያን ዘንድ በሁለቱ እንስት ስፖርተኞች መካከል ከፋተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትዕግሥት እና ሲፋን በውድድሩ ጅማሬ ላይ ከፊት ከሚመሩት ሯጮች መካከል በመሆን እስከ ውድድሩ አጋማሽ ርቀት ድረስ አብረው ቆይተዋል። 20 ኪሎ ሜትር ከተገባደደ በኋላ ግን ሲፈን ከትዕግሥት አምስት ሰከንድ ወደ ኋላ ስትቀር፣ ጄፕኮስጌይ ግን በቅርብ ርቀት ትዕግስትን በመከተል ለመፎካከር ሞክራለች።
እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ትዕግሥት እና ጄፕኮስጌይ ሳይነጣጠሉ ከሮጡ በኋላ ትዕግሥት ፍጥነቷን በመጨመር በመካከላቸው ያለውን ክፍተት በማስፋት ከኬንያዊቷ ተፎካካሪዋ ጋር ያላትን ትንቅንቅ አለዘበችው።
በዚህም ትዕግሥት የውድድሩ 40ኛ ኪሎ ሜትር ላይ ስትደርስ በመካከላቸው የነበረው የሰዓት ልዩነት ወደ 56 ሰከንድ ሰፍቶ ነበር።
በመጨረሻም ትዕግሥት አሰፋ ፓሪስ ላይ ሁለተኛ ሆና ያጣችውን አሸናፊነት ለንደን ላይ በማካካስ በ2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት ክብረ ወሰን በማሻሻል ድል አድርጋለች።
ሁለተኛ ደረጃ ላይ ኬንያዊቷ ጆይስሊን ጄፕኮስጌይን በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ፣ ኔዘርላናዳዊቷ ሲፋን ሐሰን ደግሞ በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ሦስተኛ ሆናለች።
ትዕግሥት ከድሏ በኋላ "ባለፈው ዓመት በውድድሩ ሁለተኛ ነበር የወጣሁት፤ በዚህ ዓመት ደግሞ አሸነፍኩ ይህ ልዩ ነው። በጣም ደስ ብሎኛል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ባለፈው ዓመት በነበረው ቅዝቃዜ ችግር ነበረብኝ፣ በውድድሩ መጨረሻ ላይ ታፋዬ ላይ ህመም አጋጥሞኝ ነበር። በዚህ ዓመት የነበረው አየር ሁኔታ ተመችቶኝል። በውድድሩ በጣም ነው የተደሰትኩት።"
ባለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን ውድድር የሴቶችን የማራቶን ክብረ ወሰን በከፍተኛ ልዩነት በማሻሻል ዓለምን ያስደነቀችው ትዕግሥት፣ በፓሪስ ኦሊምፒክ በጥቂት ልዩነት በሲፋን ተቀድማ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያን ብታጣም በለንደን ማራቶን አሸናፊ ከመሆን ባሻገር ክብረ ወሰን ለማሻሻል በቅታለች።
ይህም ትዕግሥት አሰፋ ባለንበት ዘመን በዓለም የሴቶች የማራቶን ውድድር ዋነኛዋ አትሌት እድትሆን በማድረግ በቀጣይ በሚኖራት ውድድር ሌላ ድል ሌላ ክብረ ወሰን እንደምታሻሽል ተጠባቂ አድርጓታል።












