በዓለም ሻምፒዮና የሚሳተፉት 90 በመቶ አትሌቶች ያደረጉት አዲሱ የፆታ ምርመራ ምንድን ነው?

ሴት አትሌቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሴቶች ዘርፍ በዓለም ሻምፒዮን የሚወዳደሩ አትሌቶች የፆታ ምርመራ ማድረግ አለባቸው

በመላው ዓለም ስፖርታዊ ውድድሮች በሴቶች ምድብ የሚወዳደሩ አትሌቶች ለአንድ ጊዜ ማድረግ ያለባቸው የጂን (ፆታ) ምርመራ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጀመሩ በፊት ተፈፃሚ መሆን ጀምሯል።

የዓለም አትሌቲክስ የዋይ ክሮሞዞም (Y chromosome) መኖርን የሚያረጋግጠው የፆታ ምርመራ የሴቶችን ውድድር ታማኝነት ለመጠበቅ ነው ይላል።

ይሁን እንጂ በጣም አከራካሪ ከሆኑ የስፖርት ጉዳዮች አንዱ የሆነውን ይህ ምርመራው እንዴት ይፈታል? እዚህ የደረሰውስ እንዴት ነው? በፆታ ጉዳይ ለሚነሳውን ክርክር አንደምታው ምንድን ነው?

ምርመራው ምንድን ነው የሚፈልገው?

ምርመራው የዋይ ክሮሞዞም አካል የሆነውን 'ኤስአርዋይ' (SRY) የተባለውን ወይም ፆታን የሚለየውን ክፍል እና የወንድነት ባህሪይ እንዲዳብር የሚያደርገውን ክፍል የሚመረምር ነው።

አንድ ጽንስ 'ኤክስዋይ' ክሮሞዞም ካለው ፆታን የሚለየው ጂን (ዘረ መል) እንደ ጥንካሬ እና ጡንቻ ያሉ የወንድ ዕድገትን የሚያመጡ የወንድነት (ቴስታስትሮን) ሆሮሞኖችን ያመርታል።

ወንድ ሆነው የተወለዱ እና በጉርምስና ያለፉ አትሌቶች ሴት ሆነው ከተወለዱት የተሻለ ሥነ አካላዊ (ፊዚዮሎጂ) ብልጫ እንዳላቸው ምርምሮች ያሳያሉ።

ምርመራው 'ፆታቸው ተለዋውጦ የተወለዱ' አትሌቶች ተፈጥሯዊ ፆታ እንዲለይ ተደርጎ የተነደፈ ነው።

ይህ ሁኔታ እምብዛም ያልተለመደ እና የአንድ ሰው ሆርሞን እና የተዋልዶ ክፍል የወንድ እና የሴት ባህሪይ ሆኖ ሲቀላቀል ማለት ነው።

አንዳንዶች በሴት ብልት ተፈጥረው ነገር ግን የወድነት ሆርሞን ያላቸው እና በአብዛኛው ሴት ተብለው የልደት ሰርተፊኬት የሚያገኙ እና እንደ ሴት እንዲያድጉ የሚደረጉ ናቸው።

'የኤስአርዋይ' ምርመራ እንዴት ነው የሚካሄደው?

ምርመራው ከአፍ ውስጥ ናሙና በመውሰድ ወይም በደም ምርመራ የሚከወን ነው። ይህ ምርመራ አትሌቶች በየአገራቸው ባሉ ብሔራዊ ፌደሬሽኖች በሕይወታቸው አንድ ጊዜ ብቻ የሚያደርጉት ነው።

በምርመራው 'ዋይ ክሮሞዞም' ኔጌቲቭ ከሆነ ወይም ባዶ ከሆነ አትሌቶቹ በሴቶች ምድብ ለመወዳደር ብቁ ናቸው ማለት ነው።

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን እንደሚለው '46ኤክስዋይ ዲኤስዲ' ከተገኘባቸው እና እነዚህ የወንድ ክሮሞዞም ያላቸው ተወዳዳሪዎች 'በኤስአርዋይ' እና በሌሎችም ጂኖች ምክንያት የተዋልዶ መራቢያ ወይም የወሲብ አካል ይኖራቸዋለ። እነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ ሴት ሆነው የተወለዱ ናቸው።

ይህ ሲፈጠር አትሌቶቹ የወንድነት ቴስታስትሮን ሆርሞናቸውን የማጥፋት ሕክምናቸውን ካጠናቀቁ እና በወንድ ጉርምስና ካላለፉ በሴቶች የውድድር መደብ ለመወዳደር ብቁ ይሆናሉ።

የዓለም አትሌቲክስ ደንቦችን የሚያከብሩ እስከሆነ ድረስ አነስተኛ የፆታ ዕድገት ለውጥ (ዲኤስዲ) ያላቸው አትሌቶች እንዲወዳደሩ ፈቅዷል።

የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሎርድ ኮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሎርድ ሴባስቲያን ኮ የፆታ ምርመራው ከአትሌቶች ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል ብለዋል

እስካሁን ምን ያህል ምርመራዎች ተደርገዋል?

የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽን እየተካሄደ ባለው የዓለም ሻምፒዮና የሚሳተፉ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አትሌቶች ምርመራ አድርገዋል።

በርካታ ምርመራዎችም በቶኪዮ ይደረጋል ተብሏል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሎርድ ሴባስቲያን ኮ የምርመራው ጊዜ የተጣበበ እንደሆነ ሳይደብቁ፤ ፈረንሳይ እና ኖርዌይን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት ለሕክምና ምክንያት ያልሆነ የጄነቲክ (የዘረ መል) ምርመራ ሕገወጥ መሆን ውስብስብ ሁኔታን መፍጠሩን ገልፀዋል።

የካናዳ አትሌቶች ቡድን "የምርመራ ስህተት" ከተፈጠረ በኋላ እና ከአፍ የሚወሰደው ናሙና መስፈርት አለማሟላቱን ተከትሎ ዳግም እንዲመረመሩ ተደርጓል።

የዓለም አትሌቲክስ ለምን አሁን ይህን ለማድረግ መረጠ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ 2009 ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴሜኒያ በርሊን በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ካሸነፈች ወዲህ ፆታ በስፖርት ውድድሮች ውስጥ ትልቅ መከራከሪያ ሆኗል።

አትሌቷ '46 ኤክስዋይ 5-ኤአርዲ' በተባለ ሁኔታ ነው የተወለደችው። ይህ ሁኔታ ያለባቸው ሰዎች የወንድ 'ኤክስዋይ' ክሮሞዞም ያላቸው እና አብዛኞቹ ሲወለዱ ሴት ተብለው ይመዘገባሉ።

በአውሮፓውያኑ 2019 የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለፍርድ ቤት ካስተር ሴሜኒያ "በተፈጥሮ ወንድ ናት" ማለቱ የተገለፀ ሲሆን፤ አትሌቷ በዚህ አስተያየት እንደተሰደበች እንደተሰማት ተናግራለች።

ሴሜኒያ በሕጋዊ የልደት ሰርተፊኬቷ ሴት ሆና የተመዘገበች ሲሆን፤ አትሌቷ ማህፀን ሳይኖራት በውስጣዊ የወንድ ብልት (ቴስቲክልስ) እንደተወለደች እና የሴት ብልት ያላት እንዲሁም ሴት እንደሆነች ተናግራለች።

በ2016 (እአአ) በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ካስተር ሴሜኒያን ጨምሮ በሴቶች 800 ሜትር ተወዳድረው ያሸነፉት ሦስቱም አትሌቶች የፆታ ዕድገት ልዩነት (ዲኤስዲ) ያላቸው ናቸው።

ይህም ሕጎችን ጠበቅ እንዲደረጉ ጥሪዎች እንዲበረቱ አድርጓል።

ከዚህም በኋላ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ400 ሜትር እስከ አንድ ማይል ላሉ የትራክ ውድድሮች ብቁ ለመሆን አትሌቶች የቴስታስትሮን መጠናቸውን እንዲቀንሱ አጥብቆ ጠይቋል።

ካስተር ሴሜኒያ ይህን ማድረግ የሰብዓዊ መብቷን የሚጥስ እና አድሏዊ አሠራር ነው በሚል አሻፈረኝ ብላለች።

ሕጋዊ ክርክሮች እየቀጠሉ ባለበት ሁኔታ የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2023 ሕጉን የበለጠ ጠበቅ አድርጓል።

የወንድ የጎረምሳነት ጊዜያቸውን አልፈው ፆታቸውን የቀየሩ አትሌቶች በሴቶች ውድድር እንዳይሳተፉ አግዷል።

የፆታ ዕድገት ልዩነት ያላቸው አትሌቶች ደግሞ ለአጭር እና ለረጅም ርቀቶች የቴስታስትሮን መጠናቸውን እንዲቀንሱ ግዴታ ጥሏል።

በ2025 መጀመሪያ ደግሞ የፌዴሬሽኑ የሥራ ቡድን የቴስታስትሮን መጠንን መቀነስ የወንዶችን አካላዊ ብልጫ ሙሉ ለሙሉ እንደማያስቀር ጥናት ማሳየቱን በመጠቆም ቁጥጥሩ ጠበቅ እንዲል ምክረ-ሃሳብ አቅርቧል።

"በትልቅ መድረክ በሴቶች ዘርፍ ለመወዳደር በተፈጥሮ ሴት መሆን አለባችሁ" ሲሉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሎርድ ሴባስቲያን ኮ ተናግረዋል።

ካስተር ሴሜኒያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ካስተር ሴሜኒያ በዓለም ሻምፒዮና በ800 ሜትር ካሸነፈች በኋላ የፆታ ጉዳይ በስፖርት አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል

ሌሎች ስፖርቶችስ?

በዚህ ዓመት የዓለም ቦክስ ፌዴሬሽንም የግዴታ የፆታ ምርመራን አስተዋውቋል።

በሊቨርፑል በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና መወዳደር ለሚፈልጉ ሴት ተወዳዳሪዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

ፌደሬሽኑ በተፈጥሮ ወንድ ሆነው የተወለዱ፣ ማለትም የ'ኤስአርዋይ' ጂን ያላቸው ወይም የፆታ ዕድገት ለውጥ ያላቸው አትሌቶች በወንዶች መደብ ለመወዳደር ብቁ ናቸው ብሏል።

በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢማን ኻሊፍ እና ሊን ኡ-ቲንግ በዓለም ሻምፒዮና የፆታ ብቁነት ምርመራን ወድቀው ማሸነፋቸው ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል።

ሁለቱም ቦክሰኞች ሲወለዱ ፆታቸው ሴት ተብሎ የተመዘገበ እና አትሌቶቹም ሴቶች እንደሆኑ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ የዓለም ቦክስ ማኅበር ኻሊፋ 'ኤክስዋይ ክሮሞዞም' እንዳላት ማሳወቁ ተፋላሚዋ የፆታ ዕድገት ልውጥ እንዳላት ጭምጭምታዎች ነበሩ።

ቢቢሲ ጉዳዩ እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጥ አልቻለም።

ኻሊፋ የፆታ ምርመራ ሕጉ እንዲቀለበስ በስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት ክስ መሥርታለች።

የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ምርመራውን ይቀበለዋል?

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የፆታ ምርመራው አትሌቶች ላይ መገለልን ወይም አድልዖን ይፈጥራል የሚል ስጋት አለው።

በ2024 ፕሬዝዳንት ቶማስ ባህ "አንዳንዶች እንደሚያስመስሉት ቀላል አይደለም። 'ኤክስኤክስ' ወይም 'ኤክስዋይ' በወንድ እና በሴት መካከል ግልፅ መስመር አይደለም። ይህ አሁን ላይ በሳይንስ እውነት አይደለም" ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ የቦክስ ውድድር በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት የሴቶች ጥቃት ልዩ ራፖርተር በሴቶች ላይ የሚደረግ የፆታ ምርመራ ዳግም እንዲጀመር ጥሪ አቅርቧል።

አዲሷ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ክሪስቲ ኮቨንትሪ የሴቶችን የውድድር ዘርፍ መጠበቅ ቅድሚያ እንደሚሰጠው የተናገሩ ሲሆን፤ በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ምርመራውን ለመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2028 በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው ኦሊምፒክ የፆታ ምርመራ በአንዳንድ ዘርፎች እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የዓለም ፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አንድሪው ፓርሰንስ ሁሉም ፌደሬሽን የየራሱን የስፖርት ዘርፍ በራሱ ሕግ መሠረት እንዲወሰን ሊያደረግ ይገባል በሚል የፆታ ብቁነት ምርመራውን "ባዶ መፍትሔ" ብለውታል።

ኒኪ ሂልትዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካዊቷ አትሌት ኒኪ ሄልትዝ

የፆታ ልየታ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ውሎ ያውቃል?

የግዴታ የክሮሞዞም ምርመራ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በ1960ዎቹ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በዓይን ፍተሻ ማድረግን ይጠቀም የነበረ ሲሆን፤ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግ እና ግላዊነትን የሚጥስ ነው የሚል ስጋት ነበረው።

በአውሮፓውያኑ 1986 ስፔናዊ የመሰናክል ሯጭ ማሪያ ሆዜ ማርቲኔዝ ፓሊኖ ምርመራውን ወድቃ ከውድድር ከታገደች በኋላ 'ኤክስዋይ' ክሮዘም ቢኖራትም አካሏ ከቴስታስትሮን አለመጠቀሙ ተረጋግጧል።

አትሌቷ ወደ ውድድር የተመሰች ሲሆን፤ የኦሊምፒክ ኮሚቴው 'ኤስአርዋይ' የጂን ምርመራ ማድረግ ቢጀምርም ሴት አትሌቶች በተፈጥሮ ሁኔታዎች እየተቀጡ ነው የሚል ስጋት አድርበታል።

በ1990ዎቹ የፆታ ማረጋገጫ ምርመራዎችን አንስቷል።

አቀባበሉ ምን ይመስላል?

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሎርድ ሴባስቲያን ኮ በአዲሱ ምርመራ አትሌቶች "ከሚጠበቀው በላይ ትብብር" ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ተሟጋቾችም የፆታ ምርመራው ዳግም መጀመሩ ዘግይቶ የመጣ መልካም ዜና አድርገው ተቀብለውታል።

"ሁሉም ስፖርት የዓለም አትሌቲክስን እና ቦክስ ፌዴሬሽንን ሊከተል ይገባል" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የፆታ ለውጥ ያደረገችው አሜሪካዊቷ ሯጭ ኒኪ ሂልትዝ ምርመራውን "የሚያበሳጭ" ያለች ሲሆን፤ "የሚያስተላልፈውን መልዕክት አልወደድኩትም" ብላለች።

ለዓለም ሻምፒዮን ያለፈችው አትሌቷ ምርመራውን ብትወስድም አካሄዱ እና የሚወጣው ገንዘብ እንዳልተዋጠላት ገልፃለች።

ከሳይንሱ እና ከአካዳሚክ ማኅበረሰቡም ቢሆንም የግዴታ ምርመራው "የተንሻፈፈ ነው" በሚል እና አትሌቶችን በፆታዊ ማንነታቸው አሳልፎ የሚሰጥ ነው በሚል የተቃወሙትም አልጠፉም።

የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የመጀመሪያ ምርመራው ፖዘቲቭ ከሆነ የብቁነት ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ትክክለኛ ውጤት ለማግኘት ተጨማሪ የሕክምና ምርመራ እንደሚደረግ ተናግሯል።

አንዳንድ ባለሙያዎች ደግሞ የፆታ ምርመራው የሕግ ፈተና እንደሚገጥመው እየተናገሩ ነው።