የሮናልዶ ‘ፖስተር’፣ ሪያል ማድሪድ፣ ፈረንሳይ - ምባፔ እና የሕይወት ዘመን ህልሙ

ኪሊያን ምባፔ ታዳጊ ሳለ

የፎቶው ባለመብት, OFFSIDE SPORTS PHOTOGRAPHY

ከፈረንሳዩ ክለብ ሞናኮ ቤተ-መዝክር ውስጥ ኪሊያን ምባፔ ታዳጊ ሳለ የተነሳው ባለ ጥቁር እና ነጭ ፎቶ አለ። ፎቶው ላይ ምባፔ ትምህርቱን በጥሞና ሲከታተል ይታያል።

ልክ እንደሌሎቹ የምባፔ የልጅነት ፎቶዎች ይህም ፎቶ የታዳጊውን ተስፋ፣ ደስታ እና ምስኪንነት የሚያሳይ ነው።

ቤተ-መዝክሩ ላይ ከተሰቀሉ የቪደዮ ካሴቶች አንዱ ደግሞ ምባፔ ሲዘል ሲጫወት ያሳያል። ሞ-ና-ኮ እያለ ይዘላል።

ታዳጊው ምባፔ እንደ ልጅነቱ ይዝለል፣ ይጨፍር፣ ይጫወት እንጂ ዐይኑ ላይ ቁም-ነገር ይነበባል። ‘ፕሮጀክት ምባፔ’ የሚል ይመስላል።

ምባፔ ገና ከልጅቱ ምን መሆን እንደሚሻ ያውቀዋል። ወደፊት እንደሚያሳካው ያውቀው ነበር ወይ? እሱን ተጫዋቹ ይመለስለዋል። ነገር ግን ህልሙ አንድ እና አንድ ነበር።

ከድሮዎቹ የቪድዮ ካሴቶች አንዱ ምባፔ የተለያዩ ቋንቋዎች በተለይ ደግሞ ስፔንኛ ሲያጠና የሚያስመለክት ነው።

“ምናልባት ወደፊት ይጠቅመኝ ይሆናል” ይላል። “ለምሳሌ ቃለ-መጠይቅ ሳደርግ በፈረንሳይኛም ሆነ በሌላ ቋንቋ ማውራቴ አስፈላጊ ነው” ሲል ገና በታዳጊነት ዘመኑ ይተልማል።

በልጅነቱ ያጠናው ስፔንኛ ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት ሊጠቅመው ይችል ይሆናል።

ከፈረንሳዩ ኃያል ክለብ ፓሪ ሳን ዠርማ ጋር ያለውን ኮንትራክት የፈፀመው የ25 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

የምባፔ ህልሙ ይህ ነበር። ገና ልጅ ሳለ የክሪስቲያኖ ሮናልዶን ግዙፍ ፎቶ ክፍሉ ለጥፎ የሚያልም የነበረው አንድ ቀን ለሪያል ማድሪድ መጫወትን ነው።

ኪሊያን ምባፔ ለሞናኮ ሲጫወት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእግር ኳስ ሕይወት ትላልቅ የሚባሉ ዋንጫዎችን የሚያነሳበት ቤትም ሊሆን ይችላል። እንደ ሮናልዶ እና ሜሲ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የሚንበሸበሽበትም መሆኑ አይቀሬ ይመስላል።

“በእግር ኳስ ሕይወቱ ቢያንስ 10 ዓመታት መጫወት ይችላል። እስካሁን ያሳካውን ስናየው እውነት አስፈሪ ነው” ይላሉ የቀድሞው የአርሰናል አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር።

ቬንገር አሁን በፊፋ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ዕድገት ኃላፊ ናቸው።

“አሁን ያለበት ደረጃ ምን መሥራት እንዳለበት የሚያውቅበት ነው። በእግር ኳስ ሕይወቱ ቁንጮ መሆን የሚችልበትም ነው። አካላዊ ጥንካሬው የሚጎመራበት ደረጃ ነው።”

ዘጠና በመቶ ያለበትን ደረጃ መጠቀም ከቻለ ምርጥ መሆን ይችላል። ከአቅሙ ምን ያህሉን ለመጠቀም አስቧል? ወደየት መጓዝ እንዳለበት ግልጽ የሆነ ምሥል አለው ወይ?”

ምባፔ እና መላ ቤተሰቡ ገና ከልጅነቱ ወደየት መሄድ እንደሚፈልጉ ያውቃሉ። በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ቁንጮ መሆን ነው ዓላማቸው።

“ኪሊያን ልጅ ሳለ እግር ኳስ እና ትምህርት ብቻ ነበር የሚያውቀው” ይላል የልጅነት ጓደኛው ራያን ቪያንጋ።

ያደገው ከፓሪስ ወጣ ብላ ባለች ከተማ ነው። ምባፔ በአውሮፓውያኑ 1998 ቦንዲ በምትባለው ከተማ ፈረንሳይ የዓለም ዋንጫን ካነሳች ከወራት በኋላ ነበር የተወለደው።

በወቅቱ ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ስታነሳ ከፓሪስ ወጣ ብለው ካሉ ከተሞች የመጡት ሊሊያም ቱራም እና ቲየሪ ሄንሪ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ነበሩ።

በ2022 ፈረንሳይ በኳታር የዓለም ዋንጫ ስትሳተፍ ከተካተቱ ተጫዋቾቹ 30ዎቹ ከፈረንሳይ ትናንሽ ከተሞች የመጡ ናቸው።

ምባፔ በ2018 የዓለም ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ካነሳ በኋለ ወዲያው ያመራው ወደ ቦንዲ ነው።

“ያደግኩበት ከተማ ነው። ተመልሼ መምጣቴ በጣም አስደስቶኛል” ሲል በወቅቱ የተቀዳ አንድ ቪድዮ ላይ ሲናገር ይደመጣል።

የምባፔ ቤተሰብ የሚኖርበት ቤት የቦንዲ ስፖርት ክለብ ሜዳን ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነው። እግር ኳስ ተጫዋች የነበሩት አባቱ ዊልፍሬድ በወቅቱ አሠልጣኝ ነበሩ።

እናቱ ፋይዛ ላማሪ የቀድሞ ፕሮፌሽናል የእጅ ኳስ ተጫዋች ናቸው። ምባፔ ልጅ ሳለ በዕድሜም በአካል እጥፍ ከሚበልጡት ጋር እየተጋፋ ኳስ ይጫወት ነበር።

“ምባፔ በዚያ ዕድሜው ከሌሎቹ የቦንዲ ተጫዋቾች ልቆ የሄደ ነበር” ይላል ቪያንጋ።

“ይህ ሕግ ነው። በወቅቱ በጣም ምርጥ ከሚባሉ ጋር መጫወት ነበር ዓላማው። አንዳንድ ጊዜ በሁለት ሜትር ከሚበልጡት ጋር ይጫወታል። አባቱ አሠልጣኝ ነበሩ። በጣም አሪፍ ከሚባሉ ተከላካዮች ተቃራኒ እንዲጫወት ነበር የሚያደርጉት።”

ታዳጊው ምባፔ እና አባቱ ዊልፍሬድ

የፎቶው ባለመብት, LIBERATION

የምስሉ መግለጫ, ታዳጊው ምባፔ እና አባቱ ዊልፍሬድ

ምባፔ የሮናልዶን ‘ፖስተር’ ሰቅሎ የድሮ የዚነዲን ዚዳን ቪድዮዎችን እየተመለከተ ቢያድግም፣ ለዚህ ለመድረሱ አስተዋፅዖ ያደረገለት ስሙ የማይታወቅ ሦስተኛ ሰው አለ።

እነ ምባፔ ቤት በማደጎ ያደገው ወንድሙ ጂሬስ ኬምቦ ኢኮኮ የ9 ዓመት ታዳጊ እያለ ነው ዊልፍሬድ እና ፋይዛ ቤታቸው ያስገቡት።

በፈረንሳይ ሊግ 1 ለሬኔ የተጫወተው ኢኮኮ፤ ምባፔን በ10 ዓመት ቢበልጠውም ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጎለታል። ምባፔ በ6 ዓመቱ የፈረንሳይን ብሔራዊ መዝሙር ሲሸመድድ “አንድ ቀን ፈረንሳይን ወክዬ በዓለም ዋንጫ እጫወታለሁ” ብሎ ለአስተማሪው ተናግሮ ነበር።

ምባፔ ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ ሙሉ እምነት የነበራቸው እናት እና አባቱ ብቻ አልነበሩም። ግዙፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ ገና የ10 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው ነፃ ጫማ አምጥተው የሰጡት።

በ16 ዓመቱ ለሞናኮ የመጀመሪያውን ጨዋታ አደረገ። ነገር ግን በ10 እና 16 ዓመቱ መካከል የነበረው ሽግግር ቀላል የሚባል አልነበረም።

ሞናኮ፤ ምባፔ የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ ነው ብቃቱን ለይተው ያስፈረሙት። አቅመ ደካማ የሚባሉ ዜጎች ከሚኖሩበት የፓሪስ ጥጋጥግ ከተማ ወደ ሀብታሞች ሰፈር መሸጋገር ለታዳጊዎች ፈተና ሊሆን ይችላል። ምባፔ ግን ይህ አልደነቀውም።

ከአራት ዓመታት በኋላ ሩሲያ ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ለአገሩ ትልቁን ድል ከማሳካቱም በላይ በፍፃሜው ጎል ያስቆጠረ ታዳጊ በመሆን የፔሌን ታሪክ ተጋራ።

በወቅቱ “የሚደንቅ ነው” ሲል ከታይም ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሮ ነበር።

“ሁሉም ታዳጊ ህልም አለው። ይህ ህልም መሳካት ሲጀምር በተለይ ደግሞ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁሉም እውን ሲሆን ማየት የሚደንቅ ነው።”

በእግር ኳስ ድንቅ ተሰጥኦ ማለት ድንቅ ገንዘብ ማለት ነው።

የፈረንሳይ እግር ኳስ ተንታኝ የሆነው ጁሊየን ሎውረንስ “በ2017 ክረምት ሪያል ማድሪድ በ180 ሚሊዮን ዩሮ ምባፔን ከሞናኮ ለማስፈረም ተስማማ” ይላል።

ምባፔ በፓሪ ሳን ዠርማ ማሊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ምባፔ በፓሪ ሳን ዠርማ ማሊያ

“ሞናኮ ለምባፔ እንዲህ አሉት ‘ይህ ለኛ በጣም ጥሩ ገንዘብ ነው። ለማድሪድ ልንሸጥህ ወስነናል።’ ምባፔ በምላሹ ‘ማንም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ሊነግረኝ አይገባም። የራሴን ዕጣ ፈንታ ራሴው ነኝ የምወስነው’ አላቸው።”

ምባፔ ፒኤስጂን ሲቀላቀል በዓለማችን እጅግ ውዱ ታዳጊ ተጫዋች ሆነ። በፓሪ ሳን ዠርማ ማሊያ በርካታ ድሎችን አሳካ።

በርካታ መገናኛ ብዙኃን ምባፔ በፓሪስ ቤት ያለውን ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። ማን መፈረም ማን መሰናበት እንዳለበት ሁሉ ይወስናል ሲሉ ፃፉ። ለራሱ ያለው ግምት በጣም ከፍ ያለ ነው ሲሉ ነቀፉት።

ነገር ግን ይህ ትችት ምባፔን የሚነቀንቀው አልሆነም። ለራሱ ያለው ግምት ከፍ ብሎ ቢገኝ እንኳ ቤተሰቦቹ እንደሚመልሱት የሚያውቁት ሰዎች ይናገራሉ።

ባለፈው ታኅሣሥ 25ኛ ዓመቱን የደፈነው ምባፔ ለክለብ እና ለብሔራዊ ቡድኑ 306 ጎሎች አስቆጥሯል። ክሪስቲያኖ በዚህ ዕድሜው 160 ጎሎችን ነው ያስቆጠረው። ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ 279 ጎሎች።

በሚመጣው ክረምት በሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ጎልተው ከሚወጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደሚሆን የሚጠበቀው ምባፔ፤ በምንጊዜም የፈረንሳይ ጎል አስቆጣሪዎች መዝገብ ላይ ሦስተኛ ነው። ምባፔ 46 ጎሎች አሉት። ቲዬሪ ሄንሪ 51፣ ኦሊቨር ዥሩድ ደግሞ 57 ጎሎች አስቆጥሯል።

በዚህ ተፅዕኖው ምክንያት የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዲዲዬ ዴሾ የቡድኑ አምበል አደረጉት።

ምባፔ በፒኤስጂ ማሊያ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። በ2020 ለፍፃሜ ደርሶ በባየርን ሚዩኒክ መረታቱ የሚታወስ ነው።

የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ብቻ ሳይሆን ባለን ደ ኦርም የዋንጫ ቁም ሳጥኑ ላይ የለም። የፊፋ ምርጡ ተጫዋችም አልተባለም። “ፕሮጀክት ምባፔ” ገና አልተጠናቀቀም ማለት ነው።

ቢሆንም ገና ጊዜ አለው። ጥማት አለው። ሪያል ማድሪድ ደግሞ ይህን ህልሙን የሚያሳካበት አልፎም የጊዜው ምርጡ ተጫዋች የሚሆንበት ሊሆን ይችላል።