ቶተንሃም ከሊቨርፑል፣ ኒውካስል ከቼልሲ እና አስቶን ቪላ ከማንቸስተር ዩናይትድ፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ቶተንሃም ከሊቨርፑል

በሳምንቱ መጨረሻ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል ኒውካስል ከቼልሲ እና አስቶን ቪላ ከማንቸስተር ዩናይትድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ።

በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ቶተንሃም ሆትስፐር እና ሊቨርፑል ቅዳሜ እንዲጫወቱ መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል።

የ17ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን እንደሚከተለው ገምቷል።

ቅዳሜ

ኒውካስል ከ ቼልሲ

ኒውካስል በበርካታ ውድድሮች የተወጠረ ሲሆን ቼልሲ ቤት ደግሞ አለመረጋጋት ይስተዋላል።

አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ሰማያዊዎቹ ቤት ውስጥ ያላስደሰታቸው ነገር እንዳለ ያስታውቃል።

ቡድኑ ኒውካስልን የሚቀጣበት ዕድል ቢኖረውም ጨዋታውን ባለሜዳዎቹ ያሸንፋሉ።

ግምት፡ 2 - 1

በርንመዝ ከ በርንሌይ

ሁለቱም ቡድኖች ያለፉትን ሰባት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። በርንሌይ ሰባቱንም ጨዋታ ተሸንፏል።

በርንሌይ ሽንፈቶችን ቢያስተናግድም በሜዳ ላይ ግን ተፎካካሪ ለመሆን እየቻለ ነው።

በርንመዝ በውድድሩ መጀመሪያ ካሳየው ጥሩ ጅምር ተንሸራቶ አሁን 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፈው ሳምንት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ተፎካክረው 4 አቻ መለያየታቸው ለዚህ ጨዋታ መነሳሻ ይሆናቸዋል።

ግምት፡ 2 - 0

ብራይተን ከ ሰንደርላንድ

ሰንደርላንድ በድንቅ አቋም ላይ ይገኛል። ይህንንም ባለፈው ሳምንት ኒውካስልን በማሸነፍ አረጋግጧል።

በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት የሚያጧቸውን ተጫዎቾች ተክተው ለሚገቡት ተሰላፊዎች ራሳቸውን ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል።

ብራይተን ከዚህ ቀደም የነበረውን አይነት ጥንካሬ እያሳየ አይገኝም።

ሆኖም ይህንን ጨዋታ ብራይተን እንደሚያሸንፍ ይሰማኛል።

ግምት፡ 1 - 0

ማንቸስተር ሲቲ ከ ዌስት ሃም

ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ላሸነፉት ሲቲዎች ይኼኛውም በቀላሉ ሦስት ነጥብ የሚያሳኩበት መርሃ ግብር ነው።

ዌስትሃም በኑኖ እስፕሪቶ ሳንቶ ስር መሻሻል ቢያሳዩም አሁንም በወራጅ ቀጠና ውስጥ ነው የሚገኙት።

ይህንን ጨዋታ ሲቲ በቀላሉ የሚያሸንፈው ይሆናል።

ግምት፡ 3 - 1

ዎልቭስ ከ ብሬንትፎርድ

ዎልቨቭሶች ባለፈው ሳምንት ከአርሰናል ጋር ጥሩ ለመፎካከር ቢሞክሩም ከሽንፈት አልዳኑም።

አሰልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ ከአምስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የቡድኑን ውጤት መቀየር ይጠበቅባቸዋል።

ብሬንትፎርድ በበኩሉ ከሜዳው ውጭ ውጤታማ አይደለም።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 1 - 1

ቶተንሃም ከ ሊቨርፑል

ይህ መርሐ ግብር ፉክክር የሚታይበት የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ምን መጠበቅ እንደሚቻል ለመገመት ይከብዳል።

ቶተንሃም በቶማስ ፍራንክ ስር ውጤታማ መሆን አልቻለም።

ሊቨርፑልም ቢሆን በተመሳሳይ የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።

በዚህ ምክንያት አንደኛው ቡድን የበላይ በመሆን ያሸንፋል ለማለት የሚከብድ ጨዋታ ነው።

ግምት፡ 1 - 1

ኤቨርተን ከ አርሴናል

ኤቨርተን ከ አርሴናል

አርሴናል ከዎልቭስ ጋር ተጫውቶ ሦስት ነጥብ ያገኘበት መንገድ ዕድለኛ ያደርገዋል። የሻምፒዮንነት ምልክት ነውን?

ቡድኑ መጥፎም ሆኖ ማሸነፍ እንደሚችል ቢያሳይም ይህንን ጨዋታ ለማሸነፍ ግን በጥሩ አቋም ላይ መገኘት ያስፈልገዋል።

ለመድፈኞቹ መልካም የሚባለው ዜና ጠንካራ የሚባሉት የኤቨርተን ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫ እና በጉዳት ምክንያት አለመሰለፋቸው ነው።

በዚህ ምክንያት አርሴናል በጠባብ ውጤት እንደሚኣሸንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ 0 - 1

ሊድስ ከ ክሪስታል ፓላስ

ሊድስ እና አጥቂው ዶምኒክ ካልቨርት-ሌዊን በጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ። ፓላስ ደግሞ የመልሶ ማጥቃት አለቃ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል።

ፓላስ ከአውሮፓ መድረክ መልስ ሲጫወት ውጤታማነቱ ይቀንሳል። በዚህ ምክንያት ጨዋታው በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1- 1

እሑድ

አስቶን ቪላ ከማንቸስተር ዩናይትድ

አስቶን ቪላ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ

ማንቸስተር ዩናይትድ ተገማች ቡድን ባይሆንም አዝናኝ መሆኑን እያሳየ ይጘኛል። ዩናይትድ ካለፉት 26 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው በቪላ የተሸነፈው። ቪላ አርሰናልን ጨምሮ ያለፉትን 9 ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል። ይህንን መርሐ ግብርም ቪላ አሸንፎ ተከታታይ 10ኛ ድል እንደሚያስመዘግብ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

ሰኞ

ፉልሃም ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

ፉልሃም እንደ አሌክስ ኢዮቢ እና ሳሙኤል ቹክዉዜ የመሳሰሉ ተጫዋቾቹን በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ያጣል። ፎረስት ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች ስድስቱን በማሸነፍ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል። ባሲ በዚህ ጨዋታ ላይ የማይሰለፍ በመሆኑ የተለየ ፎረስትን እንመለከታለን ብዬ አስባለሁ።

ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ይሆናል።

ግምት፡ 1 - 1