የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ሲሰጥ የነበረውን ከለላ አቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ በአገሪቱ ውስጥ እንዲኖሩ የፈቀደበትን አሠራር እንዲያበቃ አደረገ።
የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ መብት የሚሰጠው በአገራቸው ግጭት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌላ ለደኅንነታቸው አስጊ የሆነ የተለየ ክስተት ካለባቸው አገራት ለመጡ ስደተኞች ነው።
በዚህ የጥገኝነት መብት ውስጥ ተቀባይነት የሚያገኙ ስደተኞች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዲሠሩ እና ከአገር እንዳይባረሩ የሚያደርግ ጊዜያዊ ከለላን ያገኛሉ።
ይህ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሲሰጥ የነበረው ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ አሁን በስደተኞች ላይ ጠንከር ያለ አቋም በሚያራምዱት በፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር እንዲያበቃ ተደርጓል።
ውሳኔው ይፋ የተደረገው የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅነንት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም የመንግሥት ውሳኔዎች በሚወጡበት የፌደራል መንግሥቱ መድረክ ላይ ባወጡት ማስታወቂያ ነው።
"የአገሪቱን ሁኔታ በመመርመር እና ከሚመለከታቸው የአሜሪካ መንግሥት አካላት ጋር በመመካከር ኃላፊዋ ኢትዮጵያ ለጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን የማታሟላ ናት የሚል ውሳኔ አሳልፈዋል" በማለት ውሳኔውን አሳውቋል።
የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ሕጋዊ ጥበቃ በመጀመሪያ ለ18 ወራት ተግባራዊ እንዲሆን ለኢትዮጵያውያን መስጠት የጀመረው ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም. የወቅቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ አሌያንድሮ ሜዮርካስ ባወጡት መግለጫ ነበር።
በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የትጥቅ ግጭት፣ የተለየ እና ጊዜያዊ ሁኔታን ከግምት በማስገባት በአሜሪካ ውስጥ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ተፈቅዶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል።
ይህ ጊዜያዊ ሕጋዊ ጥበቃ ለኢትዮጵያውያን በተፈቀደበት ጊዜ ወደ 27 ሺህ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር በወቅቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ተናግረው ነበር።
የዚህ ጥበቃ ተጠቃሚ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ውሳኔው ይፋ ከመሆኑ በፊት በአሜሪካ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ወደ አሜሪካ መግባት ለዕድሉ ተጠቃሚ እንደማያደርግ ተግለጾ ነበር።
ለስደተኞች ሕጋዊ ከላለ በሚሰጠው በዚህ አሠራር ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የሌሎች በርካታ አገራት ተጠቃሚ ሆነው ቆይተዋል። በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ የሆኑት 600 ሺህ ቬንዙዌላውያን እና 521 ሺህ ሄይቲያውያን መሆናቸው ይነገራል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የአገር ውስጥ ደኅንነት ባለሥልጣናት በቅርቡ የበርካታ አገራት ዜጎችን ከዚህ ዕድል ተጠቃሚነት ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
አሁን ከከለላው ውጪ ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን ቀደም ብሎ የሄይቲ፣ የምያንማር፣ የደቡብ ሱዳን፣ የሶሪያ፣ የቬንዙዌላ እና የሶማሊያ ዜጎች ጊዜያዊ ሕግ ጥበቃው የሚሰጣቸውን ተጠቃሚነት አጥተዋል።
በዚህ ጥበቃ ሥር ሆነው በአሜሪካ ውስጥ የመሥራት እና የመኖር ዕድል አግኝተው የነበሩት ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች አገር ዜጎች ፕሬዝዳንት ትራምፕ እያካሄዱት ካለው ስደተኞችን የማባረር እርምጃ ሊጋላጡ ይችላሉ።
የትራምፕ አስተደዳር ዋነኛ ግቡ ያደረገው በአገሪቱ ያሉ ሕገወጥ ስደተኞችን በመቶ ሺዎች ከአሜሪካ ማስወጣት ከመሆኑ በተጨማሪ ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ያላቸው ሰዎችን ሰነዶች መለስ ብሎ እንሚመረምር አስታውቋል።















