በሌሎች ላይ በሯን ዘግታ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን በስደተኝነት የምትቀበለው አሜሪካ

የኮንጎ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኮንጎ ስደተኞች

ከጥቂት ወራት በፊት በኬንያ አንድ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ላይ አንድ ግለሰብ ከባለቤቱ እና ከጨቅላ ልጁ ጋር ኩርምት ብሎ ተኝቷል።

ግለሰቡ ግራ በመጋባት እና ባለማመን ስሜት ተውጦ ነበር።

ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተሰደዱት እነዚህ ቤተሰቦች ወደ አሜሪካ ለመሄድ ሲጠባበቁ ነበር።

ነገር ግን ቤተሰቡ ሁሉንም ዝግጅት አጠናቆ ወደ አሜሪካ ሊበሩ ሁለት ቀናት ሲቀራቸው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ የስደተኞችን ፕሮግራም አገዱ።

አውሮፕላኑ ሊነሳ 24 ሰዓታት ሲቀሩትም በረራቸው በድንገት መሰረዙ ለግለሰቡ ተነገረው።

"መሄጃ አልነበረኝም" ይላል ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ ተቀይሮ ፓሲቶ እንዲባል ቢቢሲን የጠየቀው ይህ ግለሰብ ንብረቱን፣ የቤት ዕቃዎቹን ሸጦ በአሜሪካ ለአዲስ ሕይወት እየተዘጋጀ ነበር።

በጦርነት የምትናጠውን ኮንጎን ሸሽተው ነበር ወደ ኬንያ የሄዱት።

የአሜሪካ ጉዞ ባይሳካም ከጦርነት የኬንያ ኑሮ ይሻለናል ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ብቸኛው ቤተሰብ አይደለም፤ ወደ አሜሪካ ለመግባት ፍቃድ አግኝተው እየተጠባባቁ የነበሩ 120 ሺህ ስደተኞች ይህ የስደተኞች ፕሮግራም በመሰረዙ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ይህ የዶናልድ ትራምፕ እርምጃ ከእሳቸው ከቀደሙ የአገሪቱ መሪዎች በእጅጉ የተለየ ነው።

በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወቅት በአውሮፓውያኑ 2024 ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አሜሪካ ገብተዋል።

ይህም በሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ከታየው ከፍተኛ ዓመታዊ አኃዝ ነው።

በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ወደ ሥልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካ መጀመሪያ" የሚለውን አጀንዳቸው ለማሳካት እና ስደተኞች ወደ አሜሪካ የሚመጡባቸውን መንገዶች ለመገደብ እጅጉኑ በፍጥነት ተንቀሳቅሰዋል።

የፍርድ ቤት ዳኛ ትዕዛዝን በመተላለፍ በኤል ሳልቫዶር ታዋቂ ወደሆነ እስር ቤት ስደተኞችን በግድ ማጋዝ፣ ከአንድ ሺህ በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ቪዛ መሰረዝ እንዲሁም ሕገወጥ የተባሉ ስደተኞች "ራሳቸው ከአገር እንዲወጡ" አንድ ሺህ ዶላር የመስጠት ውሳኔዎች ይገኙበታል።

ከአገሪቱ በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲባረሩ የተደረጉት አብዛኞቹ ከባድ ወንጀለኞች ወይም የአሜሪካን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው ሲል ድርጊቱን ደግፎ ዋይት ሐውስ ይሟገታል።

ሆኖም ከዚህ ፖሊሲያቸው በተቃራኒ ለተመረጡ ጥቂቶች ደግሞ የተለየ አሠራር ተዘርግቶላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ "የዘር መድልዎ" ሰለባ ናቸው ላሏቸው አፍሪካነርስ ተብለው ለሚጠሩት ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በመፈረም፤ "አሜሪካ መኖር ትችላላችሁ" የሚል ለየት ያለ መብት እንዲኖራቸው አድርገዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት 59 ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን ያሳፈረ አውሮፕላን ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ አርፏል። በዚህም ወቅት በውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ይህንንም "ፍትሃዊ አይደለም" ይላል ፓሲቶ።

"የፀጥታ፣ የሕክምና አጠቃላይ ዝግጅቶችን የጨረሱ 120 ሺህ ስደተኞች አሉ። ለዓመታት ጠብቀን አሁን ግን እነዚህ (አፍሪካነርስ) በሦስት ወራት ብቻ ዝግጅታቸው ተጨርሶ ሄዱ" ይላል።

ሁኔታው ፓሲቶ መውጫ እንዳጣ እንዲሰማው አድርጎታል።

በሙዚቃ ፕሮዳክሽን ሙያ ላይ የተሰማራው ፓሲቶ የቤተሰቡን ሕይወት ለማቆየት ሲል የሙዚቃ መሳሪያዎቹን በሙሉ ሸጧል።

አሁን ደግሞ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ያገኘውን ይሠራል። "በጣም ከባድ ነው" ይላል።

ትራምፕ አፍሪካነርስን በስደተኝነት ለመቀበላቸው ምክንያቱ "የዘር ፍጅት" ስጋት አለባቸው በሚል ሲሆን፤ የቅርብ አማካሪያቸው እና በትውልድ ደቡብ አፍሪካዊ የሆነው ቱጃሩ ኤለን መስክም ይህንኑ ሲያስተጋባ ይደመጣል።

በደቡብ አፍሪካ አብዛኛውን የአገሪቱን የእርሻ መሬቶች የሚቆጣጠሩት አናሳ ነጮች የዘር ፍጅት ስጋት አለባቸው የሚለው ጉዳይ መሠረተ ቢስ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ቢታመንም፤ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ መነሳቱ አልቀረም።

በተለይም ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲን ተከትሎ በአሜሪካ ውስጥ ባሉ የቀኝ ክንፍ አክራሪዎች ዘንድ እንደ አዲስ መነሳት ጀምሯል።

ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ሥርዓት ከ30 ዓመታት በፊት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬት አናሳ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።

በደቡብ አፍሪካ የነጮች ቁጥር 7 በመቶ ብቻ ቢሆንም 72 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የእርሻ መሬት ይቆጣጠራሉ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።

ራማፎሳ እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ከነጭ የመሬት ባለቤቶች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል።

ምንም እንኳን ራማፎሳ በአዲሱ ሕግ ምንም ዓይነት መሬት አልተወረሰም ቢሉም፤ ሕጉ ከጸደቀ ከቀናት በኋላ ትራምፕ ለአገሪቱ የሚሰጠውን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር እርዳታ እንዲቋረጥ አዘዋል።

ውጥረቱም ወደ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ እንዲያድግ አድርጎታል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻሀር ማሳያ የሆነው ደግሞ ራማፎሳ ወደ ዋይት ሐውስ ባቀኑበት ወቅት ነው። ትራምፕ በቀጥታ በሚተላለፍ ቴሌቪዥን ላይ ደቡብ አፍሪካ ነጮችን እያሳደደች ነው ሲሉ ራማፎሳን አፋጠዋቸዋል።

ራማፎሳ በተረጋጋ መንፈስ ይህ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን ወደ አሜሪካ በፍጥነት ወደ አሜሪካ ለማምጣት ዋይት ሐውስ የወሰደውን እርምጃ የስደተኞች ተሟጋች ቡድኖች ተችተውታል።

"እያንዳንዱ የጥበቃ፣ ከለላ የመስጠት ጉዳይ ተዓማኒ በሆነ የመሳደደድ መረጃዎች ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። በዚህ ላይ ዋነኛው የሚነሳው ጥያቄ በሕግ ፍትሃዊነት እና እኩልነት ላይ ነው" ሲሉ ግሎባል ሪፊውጂ የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አባል የሆኑት ቲሞቲ ይናገራሉ።

"ስለዚህ አንድ ቡድን የሰብዓዊ መንገዶች ከተመቻቸለት፣ የአፍጋኒስታን አጋሮቻችንም ማግኘት አለባቸው። እንዲሁም በእምነታቸው ምክንያት የሚሳደዱ እና ሌሎች ከባድ ስጋቶች የተጋረጠባቸው እና የስደተኞችን ሕጋዊ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ቤተሰቦች ይህንን ዕድል ሊያገኙ ይገባል" ይላሉ።

ትራምፕ ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል በአሜሪካ ውስጥ ላሉ አፍጋናውያን ሲደረግ የነበረውን ጊዜያዊ ጥበቃ ላለማደስ መወሰናቸው ነው።

ለዚህም "አፍጋኒስታን የፀጥታ ሁኔታዋ ተሻሽሏል እንዲሁም ምጣኔ ኃብቷ እየተረጋጋ ነው" የሚል ምክንያት ትራምፕ ሰጥተዋል።

ደቡብ አፍሪካ በዘር ላይ የተመሠረተ የወንጀል አኃዞችን ይፋ አታደርግም።

ነገር ግን የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው በአውሮፓውያኑ ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ 2004 ባለው ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ 6953 ሰዎች ተገድለዋል።

ከእነዚህ ውስጥ 12 ያህሉ የእርሻ ላይ ጥቃት ሲሆን፣ አንዱ ብቻ ነጭ አርሶ አደር ነው። ሌሎቹ 11 ሰዎች በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ ጥቁሮች ናቸው።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ በቅርብ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በታጠቁ ሚሊሻዎች መገደላቸውን እና 100 ሺህ የሚጠጉ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳያል።

የባለቤቱ ቤተሰቦች መገደላቸውን የሚናገረው ፓሲቶ ከአገሩ የተፈናቀለው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር።

እንደ ፓሲቶ ወደ አሜሪካ በስደተኝነት መሄድ ፈታኝ መሆኑ የገባቸው ከጋዛ ተፈናቅለው በአሁኑ ወቅት በግብፅ የሚኖሩት የሐማድ ቤተሰብ ናቸው።

"በትራምፕ ዘመን ይህ የማይቻል ይመስለኛል" ይላሉ አምጃድ ሐማድ።

እሱ እና ቤተሰቡ በአውሮፓውያኑ 2024 ለአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) አመልክተው የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ውድቅ መደረጉ ተነግሯቸዋል።

ትራምፕ ለደቡብ አፍሪካውያን ነጮች ከሌሎች በፈተና ላይ ካሉ ማኅበረሰቦች በላይ ማሳሰቡ ለአምጃድ ግራ አጋብቶኛል ይላሉ።

"በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ የዘር ፍጅት ስጋት ካለባቸው ለመሆኑ ፍልስጤማውያን ምን እየደረሰባቸው ነው? "ሲሉ ይጠይቃሉ።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ53 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።

ፓሲቶ የአሜሪካ ህልሙ ከደበዘዘ በኋላ በናይሮቢ ቤት አልባ ሆኖ ከቤተሰቡ ጋር ያገኘበት ያድራል።

"አንዳንድ ጊዜ ምግብ እናገኛለን። አንዳንዴም እናጣለን። በከባዱ እየታገልን ነው" ይላል።

ትራምፕ ፖሊሲያቸውን ይቀይራሉ በሚለው ላይ የተመናመነ ተስፋ ያለው ፓሲቶ ነገር ግን እንደገና ወደ አገሩ መመለስ የማይታሰብ ሆኖበታል። "አልመለስም" ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።