አሜሪካ በየዓመቱ የምታካሂደውን የዲቪ ሎተሪ አቆመች

የዲቪ ሎተሪ

የፎቶው ባለመብት, usembassy

የምስሉ መግለጫ, የዲቪ ሎተሪ ፕሮግራሙ በአሜሪካ በስደተኝነት በቂ ድርሻን ላላገኙ አገራት ዜጎች በየዓመቱ 50 ሺህ ቪዛዎችን ይሰጣል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በብራውን ዩኒቨርሲቲ በተፈጸመ የጅምላ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የአሜሪካን ግሪን ካርድ ሎተሪን (ዲቪ) አገዱ።

ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው እና ሐሙስ ዕለት ሞቶ የተገኘው ፖርቹጋላዊው በአውሮፓውያኑ 2017 ዲቪ ሎተሪ አሸንፎ ወደ አገሪቱ የገባ ሲሆን ግሪን ካርድም ተሰጥቶታል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር የሆኑት ክሪስቲ ኖም "በዚህ አስከፊ ፕሮግራም አሜሪካውያን ከእንግዲህ እንዳይጎዱ ለማረጋገጥ" በሚል ትራምፕ በሰጡት መመሪያ መሠረት የቪዛ መርሃ ግብሩን ለጊዜው እንዲቋረጥ መደረጉን ተናግረዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተጠርጣሪው የ48 ዓመቱ ክላውዲዮ ኔቭስ ቫለንቴ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ፕሮፌሰር ኑኖ ሉሬሮንም ገድሏል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የዲቪ ሎተሪ ፕሮግራሙ በአሜሪካ በስደተኝነት በቂ ድርሻን ላላገኙ አገራት ዜጎች በየዓመቱ 50 ሺህ ቪዛዎችን ይሰጣል። ይህ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነትን ለማግኘትም በር ከፋች ነው።

ኖም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትራምፕ ቀደም ሲል በኒው ዮርክ ከተማ ስምንት ሰዎች በጭነት መኪና ተገጭተው ከተገደሉ በኋላ ፕሮግራሙን ለማስቆም "ታግለዋል" ብለዋል።

ኖም እንዳሉት የኡዝቤኪስታን ተወላጅ የሆነው ሳይፉሎ ሳይፖቭ፣ የኢስላሚክ ስቴት ደጋፊ የሆነ እና ለተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ግለሰብ በዲቪ1 ፕሮግራም መሠረት ወደ አሜሪካ ገብቷል።

ኃላፊዋ የፕሮግራሙን መቋረጥ ይፋ ያደረጉት የብራውን ዩኒቨርስቲ ጥቃት ፈጻሚ ነው የተባለው ኔቭስ ቫለንቴ በሳሌም፣ ኒው ሃምፕሻየር በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ሞቶ ከተገኘ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

ፖሊስ ግለሰቡ ሕይወቱ ያለፈው ራሱ ላይ በመተኮስ ባደረሰው ጉዳት ሊሆን አንደሚችል አስታውቋል።

የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፖሊስ ከሕዝብ የተላኩ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እና ጥቆማዎችን በመጠቀም መርማሪዎቹን ወደ መኪና ማከራያ ከላከ በኋላ የተጠርጣሪውን ስም ማግኘት መቻሉን ይፋ አድርጓል።

ለስድስት ቀን ያህል ግለሰቡን ሲፈልግ የነበረው ፖሊስ በስተመጨረሻም ተፈላጊው ግለሰብ በዚህ ስፍራ እንደሚገኝ ማረጋገጥ ችሏል።

አንድ ሻንጣ እና ሁለት የጦር መሳሪያዎች ከተጠርጣሪው አስከሬን ጎን ተገኝቷል።

በአቅራቢያው ባለ መኪና ውስጥ የተገኙ ቁሰቁሶች ከብራውን ዩኒቨርሲቲ ከተሰበሰቡ ማስረጃዎች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን የሮድ አይላንድ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፒተር ኔሮንሃ ተናግረዋል።

የብራውን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ክርስቲና ፓክስሰን እንዳሉት ኔቭስ ቫለንቴ ስመ ጥር በሆነው ትምህርት ቤት ተመዝግቦ በፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪውን ለማግኘት እየተማረ ነበር።

"ከብራውን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት" እንደሌለው ጨምረው ገልጸዋል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ኔቭስ ቫለንቴ ሰኞ ዕለት የ47 ዓመቱን የማሳቹሴትስ ኢኒስቲቲዩት ኦፍ ኢኒስቲቲዩት (ኤምአይቲ) ፕሮፌሰር ኑኖ ኤፍ ጎሜስ ሉሬሮ ከፕሮቪደንስ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ብሩክሊን በሚገኘው ቤታቸው ተኩሶ ገድሏል ብለው ያምናሉ።

ሁለቱም ሰዎች በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ በፖርቹጋል በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተምረው እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት የተጠርጣሪው ተሽከርካሪ በደኅንነት ካሜራ መታየቱን እና በብራውን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ አንድ የዐይን ምስክር ከሰጡት ቃል በመነሳት ተጠርጣሪው ወንጀሉን መፈጸሙን ማመናቸውን ተናግረዋል።

ይኸው መኪና ፕሮፌሰሩ በጥይት በተገደሉበት ቦታ አቅራቢያ ታይቶ ነበር።

ባለሥልጣናት ለሁለቱም ጥቃቶች ለመፈጸም ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ይፋ አላደረጉም።

በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 13/2025 አንድ ታጣቂ በብራውን ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርት ክፍል ሕንፃ ውስጥ በመግባት ተኩስ ከፍቶ ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ ሌሎች ዘጠኝ ደግሞ ቆስለዋል።

አሜሪካ ከአውሮፓውያን አቆጣጠር 1995 ጀምሮ በዲቪ ሎተሪ አማካኝነት ወደ አገሯ በርካቶች እንዲገቡ የምትፈቅድ ሲሆን የዲቪ 2027 ማመልከቻ ጊዜ ዘግይቶ ነበር።

የዘንድሮ አመልካቾች 1 ዶላር እንዲከፍሉ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከተለመደው የማመልከቻ ጊዜ ስለዘገየበትም ሆነ ስለክፍያው በይፋ የተነገረ ነገር የለም።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያየ እርምጃ ወስደዋል።

በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሰነድ አልባ ስደተኞችንም ወደ መጡበት ለመመለስ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ነው።

ባለፉት ሳምንታት አንድ የአፍጋኒስታን ስደተኛ በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ አባላትን በጥይት ተኩሶ አንዷን ከገደለ እና ሌላኛውን ካቆሰለ በኋላ የትራምፕ አስተዳደር ከ19 አገሮች የመጡ ስደተኞች የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ላይ ዳግም ፍተሻ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ የበርካታ አገራት ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት በማቆም የሕገወጥ ስደተኞችን ቁጥር የሚገድብ ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።