ቻይና በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የሚደረግ 'ጣልቃ ገብነትን' እቃወማለሁ አለች

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ፤ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮች የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አገራቸው እንደምትቃወም መናገራቸው ተዘገበ።

በቻይና መንግሥት የሚተዳደረው ዢንዋ የዜና ወኪል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ይን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ቻይና በኢትዮጵያ ጉዳዮች የውጭ ጣልቃ ገብነትን ትቃወማለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ነው።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንንም በትዊተር ገጻቸው "ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ጋር ባደረግነው ፍሬያማ የስልክ ውይይት የአገር ውስጥ ጉዳዮቻችንን ያለ ጣልቃ ገብነት ስለመፍታት ተነጋግረናል" ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ ባደረጉት ውይይት አገራቱ "ሉዓላዊነታቸውን እንደሚያከብሩ" እንዲሁም "እርስ በእርስ ለመተባበር ቁርጠኛ እንደሆኑ" መስማማታቸውን አቶ ደመቀ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።

ዢንዋ፤ የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዋንግ ይ "ሁለቱ አገራት የሚተባበሩ አጋሮች ናቸው" ማለታቸውን ዘግቧል።

ምዕራባውያኑ አገራት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን፣ ሕዝቡ ለረሃብ መጋለጡን፣ ሰብዓዊ እርዳታ በአግባቡ አለመድረሱን እና ሌሎችም ችግሮችን በመግለጽ የኢትዮጵያን መንግሥት መተቸት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ትችት አጣጥሎ፤ ምዕራባውያን በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ይሞክራሉ ሲል በተደጋጋሚ ተቃውሞውን ሲያሰነማ ቆይቷል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ትግራይን በተመለከተ ባደረጉት ውይይት የግድያ፣ የመድፈር፣ ለስደት የመዳረግ እንዲሁም እንደ ሕክምና መስጫ ያሉ መሠረተ ልማቶችን የማውደም ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋሞች እንዲሁም የረድኤት ድርጅቶችም ተመሳሳይ ስጋት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ይገልጻል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የተለያዩ አገራት ያሳዩትን አቋም "የኢትዮጵያን ክብር ያልጠበቀ" ብለው መግለጻቸው ይታወሳል።

ዢንዋ በድረ ገጹ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና መረጋጋቷን የመጠበቅ መብት አላት" ማለታቸውን አስነብቧል።

"ኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳዮቿን በዋነኛነት በራሷ ጥረት መፍታት አለባት። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ፍቃድ አክብሮ ድጋፍ መስጠት ነው ያለበት። ማዕቀብ መጣልም የለበትም" ማለታቸውም ተዘግቧል።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት አባሎች፣ በአማራ ክልል ኃይሎች እንዲሁም በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏ አይዘነጋም።

ለዚህም በምክንያትነት የቀረበው በትግራይ ክልል የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል፣ የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት አለማግኘቱ ነው።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ "ቻይና በትግራይ ክልል ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማርገብ እርዳታ ለመስጠት ፍቃደኛ ናት። የመጀመሪያው ዙር የምግብ እርዳታም ተልኳል" መባሉን ዢንዋ ዘግቧል።

አቶ ደመቀ፤ ቻይና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲን በማራመዷ ማመስገናቸውንም ዘገባው አስነብቧል።

ከወራት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ ውይይት በተደረገበት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትን ደግፈው ከቆሙ አገራት መካከል በምክር ቤቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላት ቻይና አንዷ ነበረች።