የታዋቂው አደገኛ ዕፅ ነጋዴ ኤል ቻፖ ሚስት ጥፋተኛ መሆኗን አመነች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የታዋቂው ሜክሲኳዊ አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪ ዮዋኪን "ኤል ቻፖ" ጉዝማን ሚስት ጥፋተኛ መሆኗን በችሎት ፊት አምናለች።
የኤል ቻፖ ሚስት በአበይትነት አደገኛ ዕፅ ለማዘዋወር አሲረሻል በሚል ክስ ነው ፍርድ ቤት ቀርባ የነበረው።
ዋሺንግተን የሚገኝ ፍርድ ቤት የቀረበችው ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ ብዙ አፍ የሚያስዙ ጉዳዮችን አምናለች።
ኤማ፤ ኤል ቻፖ ጉዝማን ከእሥር ቤት እንደሚያልጥ አግዣለሁ፤ የሲናሎዋ የዕፅ አዘዋዋሪዎች 'ንጉሥ' እያለ ረድቸዋለሁ ብላለች።
የ31 ዓመቷ ኤማ የዕድሜ ልክ እሥራት እንዲሁም የ10 ሚሊዮን ብር ቅጣት ይጠብቃታል።
በአንድ ወቅት ሜክሲኮና አሜሪካን በዕፅ ንግዱ ያሸበረው የ63 ዓመቱ ጉዝማን በዕፀ ፋርስና ሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የዕድሜ ልክ እሥራቱን ኮሎራዶ የሚገኝ ማረሚያ ቤት 'እያጣጣመ' ይገኛል።
የጉዝማን ሚስት ኤማ ፍርድ ቤት የቀረበችው አረጓንዴ ቱታና ነጭ ጭምብል አጥልቃ ነው።
በተከሰሰችባቸው ሶስት መዝገቦች ጥፋተኛ መሆኗን ያመነችው ኤማ "ሕገ ወጥ ዕፅና ገንዘብ እንዲዘዋወር አሴር ነበር፤ የሲናሎዋ ዕፅ ንግድ ላይም እጄ አለበት" ብላለች።
አልፎም ኤል ቻፖ ጉዝማን በፈረንጆቹ 2015 ከእሥር ቤት አምልጦ ዓለምን ጉድ ያሰኘበትን ድርጊት ማገዟን አምናለች።
"ሁሉንም ነገር ጥላ ወደ ፊት ለመጓዝ በማሰቧ ደስተኛ ናት" ብለዋል የተከሳሿ ጠበቃ ጄፍሪ ሊክትማን።
አስገራሚ ክስተት
የቢቢሲ የዋይት ሃውስ ወኪል የሆነችው ታራ ማኬልቪ የፍርድ ሂደቱን በአካል መታደም ችላ ነበር። እነሆ የታዘበችው፡
ድምጿ ቀዝቀዝ ቢልም በግልፅ ይሰማ ነበር።
ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው ችሎት በስፓኒሽ ጉዷን ስትዘርዘር ተሰምታለች። የትርጉም ሠራተኛዋ ደግሞ ወደ እንግሊዝኛ ስታመጣው ነበር።
በጣም አስገራሚ ክስተት ነበር። ኤማን አግኝቻት አውቃለሁ። በዕፅ ንግድ ላይ ከተሰማሩ ኃያል ሴቶች መካከል ነበረች።
ያገኘኋት ኒው ዮርክ ውስጥ ባለቤቷ ዳኛ ፊት ቆሞ ሃጢያቱን ሲናዘዝ ለመስማት በመጣችበት ወቅት ነው።
ያኔ ፎቶግራፈሮች የሷን ፎቶ ለማንሳት እየተሻሹ ወደሷ ሲመጡ በፈገግታ ነበር የተቀበለቻቸው። አሁን ደግሞ የራሷን ሥራ በዳኛው ፊት መስክራለች።
የፍርድ ሂደቱን ከችሎቱ ውጭ ካለ ክፍል ውስጥ ሆነን በስልክ መስመር ነበር የምናደምጠው።
"ጥፋተኛ ሆነሽ ተገኝተሻል" አሉ ዳኛው። የስልክ መስመሩም ተቋረጠ።
ኤል ቻፖ ጉዝማን በ2019 ስለፈፀመው በደል ችሎት ፊት ቆሞ ሲመሰክር ዓለም ጉድ ነበር ያለው።
ጉዝማን በዕፅ አዘዋዋሪነት ሕይወቱ ዕድሜያቸው 13 ዓመት የሆናቸው ታዳጊ ሴቶችን ጭምር አደንዝዞ እንደደፈራቸው እንዲሁም ተቀናቃኞቹን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደላቸው አምኗል።
የቀድሞ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ የሆነችው ኤማ ኮሮኔል አይስፑሮ ባለፈው የካቲት ነው ዋሺንግተን ውስጥ ካለ አየር ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋለችው።
አል ቻፖ እንዴት አመለጠ?
አቃቤ ሕግ በፈረንጆቹ ከ2012 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ጉዝማን ዕፅ እንዲያዘዋውር ረድታለች፤ አልፎም በ2015 ከእሥር ቤት እንዲያመልጥ አግዛዋለች ሲሉ ነበር የከሰሷት።
ጉዝማን ጠንከር ያለ ጥበቃ ካለው የሜክሲኮ አልቲልፕላኖ እሥር ቤት ያመለጠው ውስጥ ለውስጥ በተቆፈረ ቱቦ ነው።
የጉዝማን ልጆች እሥር ቤቱ አቅራቢያ ያለ አንድ መሬት ይገዛሉ። ከዚያም አቅጣጫ ጠቋሚ ሰዓት ወደ ውስጥ ያስገባሉ። ቆፋሪዎቹ ይህን ተጠቅመው ቦያቸውን ይቀዳሉ።
የውስጥ ለውስጥ መስመሩ ከተቆፈረ በኋላ ለኤል ቻፖ ተብሎ በተዘጋጀ ልዩ ብስክሌት ጉዝማን ሹልክ ይላል።
የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚያሳዩት ኤማ፤ ኤል ቻፖ ለዩናይትስ ስቴትስ መንግሥት ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት ከእሥር ቤት እንዲያመልጥ ስታቅድ ነበር።
የአሜሪካና የሜክሲኮ ዜግነት ያላት ኤማ የቀድሞ ቁንጅና ውድድር አሸናፊና የጋዜጠኝነት ትምህርት የወሰደች ናት።
ከኤል ቻፖ ጋር ባላት ትዳር መንታ ልጆች የወለደችው ኤማ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዕፅ ዝውውር ንጉሡ ጋር የተገናኘቸው እሷ 17 እሱ ደግሞ 49 እያለ አንድ የዳንስ መድረክ ላይ እንደሆነ ይነገራል።
ኤል ቻፖ የፍርድ ሂደት ላይ እያለ ችሎት ፊት ቀርባ በመሰከረች ወቅት ነው የመገናኛ ብዙሃን ዓይን ውስጥ የገባችው።
ኤማ ኮሮኔል 2007 ላይ ጉዝማንን ስታገባው ገና 18 ዓመት አልሞላትም ነበር።
አባቷ ደግሞ የጉዝማን ሉቴናንት ነበሩ። ከ6 ዓመታት በኋላ ግን በሜክሲኮ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ጉዝማን፤ ሲናሎዋ በተሰኘችው የሜክሲኮ ዕፅ ንግድ መሠረት ናት ተብላ ከምትጠራው ከተማ ከሚኖሩ ደሃ እናትና አባት የተገኘ ሰው ነው።
ጉዝማን በአንድ ወቅት አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት አለው ተብሎ በፎርብስ መፅሔት ላይ ስሙ ሰፍሮ ነበር።












