ትግራይ፡ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ በቂ እርዳታ ባይቀርብም የመንግሥት ጥረት የሚበረታታ ነው አለ

የጸጥታው ምክር ቤት (ከሌላ ስብሰባ ላይ ተወሰደ ፎቶ)

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የጸጥታው ምክር ቤት (ከሌላ ስብሰባ ላይ ተወሰደ ፎቶ)

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በቂ የሰብዓዊ እርዳታ ባይቀርብም የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት ግን የሚበረታታ ነው አለ።

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሳስቦኛል ያለ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባል አገራት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነትን ያከብራሉ ብሏል።

የመግለጫውን መውጣት ተከትሎ የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ፤ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ለሰጡት 'ገንቢ ምልከታ እና ድጋፍ' አድናቆቱን ገልጿል።

የጸጥታው ምክር ቤት ምን አለ?

የጸጥታው ምክር ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ፤ የምክር ቤቱ አባል አገራት በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ እንዳሳሰበው ገልጾ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብሏል።

የጸጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተባበሩት መንግሥታት መርህ መሠረት መቀጠል አለበትም ብሏል።

በትግራይ ያለው የደኅንነት እጦት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረም ነው ብሏል።

ጾታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ያሳስቡኛል ያለው ምክር ቤቱ፤ ጥሰቶቹ በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ እና ተጠያቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በጋራ የሚያደርጉትን ምርመራ በበጎ ጎኑ ተቀብሎታል።

የጸጥታው ምከር ቤት ዓለም አቀፍ ሕግጋቶች መከበር አለባቸው ብሏል።

ምክር ቤቱ እንደ የአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ የመሳሰሉ አህጉራዊ እና ቀጣናዊ ተቋማት ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት ለሚኖራቸው ተሳትፎ ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው ገልጿል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የፖለቲካ ነጻናትና የግዛት አንድነትን እንደሚያከብር ገልጿል።

line

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ መግለጫ ለማውጣት በርካታ ጊዜ ቢሰበሰብም ከስምምነት ሳይደርስ መቅረቱ ይታወሳል።

የካቲት 25/2013 ዓ.ም የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያደረገው ውይይት ከስምምነት ላይ ሳይደርስ መቅረቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

የዜና ወኪሉ የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ መልኩ በትግራይ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ እና ግጭት እንዲቆም የሚጠይቅ መግለጫ ለማውጣት ያደረገው ስብሰባ በሩሲያ እና በቻይና ተቃውሞ ሳይወጣ ቀርቷል።

ሩሲያ እና ቻይና መግለጫው በኢትዮጵያ "ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" በማለት ነበር ተቃውሟቸውን ያሰሙት።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አሜሪካ በሉአላዊ አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ጠይቆ ነበር።

ሩሲያቻይና በተቃወሙት ሰብሰባ ላይ ሌሎች አባላት ምን ብለው ነበር?

የካቲት 25/2013 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ውይይት ላይ በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ለሁለት ሰዓት ያህል የዘለቀ ውይይት ተካሂዶ እንደነበረ ቢቢሲ ያናገራቸው በውይይቱ ላይ የታደሙ አንድ ዲፕሎማት አስታውሰዋል።

አስራ አምስቱም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ሁሉም በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ በተመለከተ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በዝግ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ሊባል በሚችል ደረጃ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸውን ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።

ኬንያ፣ ቱኒዚያና ኒጀር እንዲሁም ሴንት ቪንሰንት እና ግሪናዲስ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ ፈቃድ የመስጠት ሂደቱን በማፋጠንና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር በኩል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ነበር።

በስብሰባው ላይ በትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ጉዳያ ሊሆን ይችላል ያለችው ፈረንሳይ ናት።

ስለዚህም ምክር ቤቱ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረጉ ቀጠናዊ ጥረቶችን ከመደገፍ በተጨማሪ ለመፍትሔው አስተዋጽኦውን እንዲያበረክት ጠይቃ ነበር።

ዩናይትድ ኪንግደም በስበሰባው ላይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማማጣት ባለመቻሉ ውጥረቱ እየተባባሰ እንዲሄድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሳ፤ የጸጥታው ምክር ቤት ይህ ቀውስ እንዲያበቃ ለማድረግ ተገቢውን ሚና መጫወት ይኖርበታል ብላለች።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ እርዳታና የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እንደሚያሳስባት ገልጻ ይህም ለቀጠናው ሰላምና ጸጥታ ቀጥተኛ ስጋት ስለሆነ በቶሎ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብላ ነበር።

ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድና ቬትናም ያለው የሰብአዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው የገለጹ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ረገድ እርዳታ ለማቅረብ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም እነዚህ አገራትና የምክር ቤቱ አባል የሆኑ የአፍሪካ አገራት ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ኢጋድንና የአፍሪካ ሕብረትን የመሳሰሉ ተቋማት ሚና እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ግድያዎችን በተመለከተ የሚወጡት ሪፖርቶች አሳሳቢ እንደሆኑ ገልጾ፤ የሰብአዊ ሁኔታውን በተመለከተ ያለው መረጃ መሬት ላይ ያለው እውነታ ነጸብራቅ እንደሆነ ገልጿል።

በተጨማሪም አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፉ ከፍ እንዲል ተጨማሪ ሐብት እንደሚያስፈልግም አመልክቷል።

የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የትኞቹ ናቸው?

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት አሉ።

ከ15ቱ አባል አገራት አምስቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ሲሆኑ፤ አስሩ ደግሞ በየዓመቱ የሚቀያየሩ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም የሌላቸው አባል አገራት ናቸው።

ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግድ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።

ኢስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ፣ ኒጂር፣ ኖርዌይ፣ ሴንት ቪንሰንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስ፣ ቱኒዚያ እና ቬትናም ደግሞ አስሩ ተለዋዋጭ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።