ኬንያ ጂቡቲን ረትታ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት መቀመጫን አገኘች

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጉባኤ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

ኬንያ ጂቡቲን በድምፅ ብልጫ ረትታ አፍሪካን በመወከል የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የተለዋጭ አባልነት አግኝታለች።

በድምፅ አሰጣጡም መሰረት ኬንያ 129 ድምፅ ያገኘች ሲሆን የጂቡቲ ደግሞ 62 ነው።

በመጀመሪያ ዙር 128 ወይንም 2/3 ድምፅ ማግኘት ሃገራቱ ተስኗቸው ነበር።

ከአራት አመታት በፊትም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ያልሆነ አባልነትም ተመርጣ ነበር። በወቅቱም በ185 ድምፅ አሸንፋለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ሶስት ጊዜ የምክር ቤቱ ቋሚ ያልሆነ መቀመጫን አግኝታለች። ከዚህ ቀደም በአፄ ኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግሥታትም ነው።

የምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር ኬንያ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ቋሚ ያልሆነ መቀመጫ የነበራትን ደቡብ አፍሪካንም ትተካለለች።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ሃገራቸው ማሸነፏንም ተከትሎ "ሃገሪቷ እያደገችበት ያለውን እንዲሁም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ በልማት አጋርነቷ እየፈጠረች ያለውን እመርታ አሳይ ነው" ብለዋል።

ጂቡቲንም በጥሩ ተፎካካሪነቷ ያመሰገኗት ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ህብረትም ድጋፍ ስለቸራቸው አመስግነዋል።

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ አፍሪካ እንደ አህጉር በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን ተሰሚነት መጨመር እንዲሁም ለጉባኤው ምርጫ ሲንቀሳቀሱበት የነበረውን ባለ አስር ነጥብ አጀንዳም እንደሚያስተዋውቁ ተናግረዋል።