ብሊንክን በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ደቅኗል ስላሉት አደጋና የአጎዋ እግድን በተመለከተ ተናገሩ

Antony Blinken

በአፍሪካ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ኬንያ ናይሮቢ የቆዩት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋት የአገራቸው ዋነኛ ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።

ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ ተቀስቅሶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋው ግጭት ስለደቀነው አደጋ እና ኢትዮጵያ ከአጎዋ የንግድ ተጠቃሚነት እንድትወጣ በአሜሪካ መንግሥት የተላላፈውን ውሳኔ በተመለከተ ለቢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

'የግጭት መስፋፋት ኢትዮጵያን የመበታተን ኃይል አለው'

አንቶኒ ብሊንክ እየተካሄደ ያለው በፌደራሉ መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የሚደረገው ጦርነት ተስፋፍቶ የሚቀጥል ከሆነ አገሪቱ የመበተን አደጋ እንደሚጋረጥባት አመልክተዋል።

"ሁለቱ ወገኖች (የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት) ለችግሮቻቸው ወታደራዊ መፍትሔ አለው ብለው ከሳቡ የግጭት መስፋፋትን እንመለከታልን" ያሉት ብሊንክ የግጭቱ መስፋፋት፤ "ኢትዮጵያን የመበታተን ኃይል አለው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ይህ አገሪቱ ላይ የተደቀነው አደጋ ለእኛ ብቻ ሳይሆን በቀጠናው እና በመላው ዓለም ላሉ አገራት እጅግ አሳሳቢ ነው" ሲሉ የአሜሪው የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አብራርተዋል።

ይህን በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች የተስፋፋውን ጦርነት በዲፕሎማሲያዊ ጥረት የማስቆም ተስፋ አለ ወይ? ተብለው የተጠየቁት ብሊንክ፤ "በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጦርነቱን በውይይት ማስቆም እንደሚቻል የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ" ብለዋል።

ብሊንከን በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያደርጉትን ጥረት አገራቸው እየደገፈች መሆኑን አመልክተዋል።

"የኦባሳንጆ፣ የፕሬዝዳንት ኬንያታ እና ሁለቱን ኃይሎች ለማቀራረብ ከሚሰሩ ሌሎች መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት አለን" ሲሉ ብሊንክን ተናግረዋል።

ኦባሳንጆ በአዲስ አበባ ካሉ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንዲሁም ወደ መቀለ ተጉዘው ከህወሓት መሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

ኦባሳንጆ የሁለቱን አካላት መሪዎች ካነጋገሩ በኋላ የማደራደር ጥረቴን አልቀበልም ያለ አካል የለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

እንዲሁም የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ባለፈው እሁድ ለአጭር ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝተው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ተዋጊ ኃይሎች የተኩስ አቁም አድርገው ልዩነቶቻቸውን በድርድር ይፈታሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጭምር ተናግረዋል።

"ሁለቱ ኃይሎች ልዩነታቸውን በንግግር ለመፍታት የተኩስ አቁም አድርገው ቁጭ ብለው በመነጋገር፤ ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን አረጋግጠው፤ ለዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ይደራደራሉ የሚል ተስፋ አለኝ።"

የአሜሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ዕድል-አጎዋ

የአፍሪካ አገራት ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ ከሚያስገቡበት በምኅጻረ ቃሉ አጎዋ ተብሎ ከሚታወቀው የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ የንግድ መርሃ ግብር ኢትዮጵያን በቅርቡ ማገዷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በአጎዋ አማካኝነት ከፍተኛ ቁጥር ላለቸው ዜጎቿ የሥራ ዕድል ከመፍጠሯ ባሻገር አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ከአሜሪካ ገበያ ስታገኝ ቆይታለች።

ይሁን እንጂ የአሜሪካ መንግሥት ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል በሚል ምክንያት ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጀምሮ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት አግዳለች።

ብሊንከንም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምትፈጽም አገር ከአጎዋ ስምምነት ተጠቃሚ መሆን የለባትም በማለት የመንግሥታቸውን ውሳኔ ትክክለኛነት አስረድተዋል።

"በአጎዋ ስምምነት መሠረት በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ የተሳተፈች አገር ከስምምነቱ ተጠቃሚ እንደማትሆን ተመልክቷል" ያሉት ብሊንከን፤ "በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው ችግር የሚቀጥል ከሆነ ከጄነዋሪ 1 (ታህሳስ 23) ጀምሮ በሕጉ መሠረት አጎዋ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅም ማንሳት አለብን" ብለዋል።

ኢትዮጵያን ከአጎዋ የማስወጣት ውሳኔ ቀጥተኛ ተጎጂዎች ተፈጽመዋል ከተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ግንኙት የሌላቸው ለፍተው የሚያድሩ ሴቶችና ተራ ዜጎች መሆናቸውን በማስታወስም የአሜሪካ ውሳኔ ትክከለኛነት ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ፡

"በዚህ ውሳኔ በቀጥታ ለሚጎዱ ሰዎች እናዝናለን። ቀድሞውኑ በጦርነቱ ምክንያት በርካቶች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ለማረጋገጥ ስንጥር ነበር፤ ለመብታቸው ስንከራከር ነበር። ይህ ግን የአገሪቱ መሪዎች ጉዳይ ነው። . . . ስለ ሕዝባቸው ኃላፊነት የሚወስዱት መሪዎቹ ናቸው።"

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በተመለከተ በቅርበት የሚከታተሉ ልዩ መልዕክተኛ ሰይማ ጥረት ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል። ልዩ መልእክተኛው ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ቀጠናው በተደጋጋሚ የተመላለሱ ሲሆን ስለደረሱበት ውጤት አስካሁን ተባለ ነገር የለም።

የውች ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ በመጓዝ ያደረጉት ያለው ጉብኝትን በኬንያ የጀመሩ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራቱ ናይጄሪያና ሴኔጋል ያቀናሉ።