ከቀናት በፊት ከኬንያው እስር ቤት ያመለጡት የሽብር ወንጀል ፍርደኞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቀናት በፊት ከኬንያው እስር ቤት ያመለጡት በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው ሦስት እስላማዊ ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ያመለጡት ሦስቱ ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ምሥራቅ ኬንያ ላይ ወደ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ለመሻገር ጥረት ሲያደርጉ ነው ተብሏል።
አደገኛ የተባሉት ሙሽራፍ አብደላ፣ ጆሴፍ ጁማ እና ሞሐመድ አሊ አቢካር በመዲናዋ ናይሮቢ አቅራቢያ ከሚገኘው እና ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት ያመለጡት ባለፈው እሁድ ነበር።
ሞሐመድ አሊ አቢካር እአአ 2015 ላይ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ በደረሰው የሽብር ጥቃት ተሳታፊ ነው ተብሎ የ41 ዓመት እስር ተፈርዶበታል። በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃት ከ148 ሰዎች በላይ ተገድለዋል።
የኬንያ ባለሥልጣናት እስረኞቹ ሊያመልጡ የቻሉት በእስር ቤቱ ውስጥ ባለው ቸልተኝነት እና የብቃት ማነስ ችግር ነው ብለው ነበር። ይህን ተከትሎ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ የአገሪቱን የማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ከሥራ አባረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና እስረኞቹ ያመለጡበት እስር ቤት ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ዴይሊ ኔሽን የተባለው የኬንያ ጋዜጣ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ፍርደኞች ፎቶ አጋርቷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ሦስቱን እስረኞች መልሶ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የአገሪቱ ፖሊስ አገር አቀፍ ፍለጋ ጀምሮ ነበር። ሦስቱ ግለሰቦች ያሉበትን ለጠቆመም 20 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ (ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ) በሽልማት እንደሚሰጥ ባለሥልጣናት አስታውቀው ነበር።
ከእስር ያመለጠው ሁለተኛው ወንጀለኛ እአአ 2012 በኬንያ ፓርላማ ላይ ጥቃት ለማድረስ ታስቦ ሳይሳካ ከቀረው ሙከራ ጋር በተገናኘ የተያዘ ነው። ሦስተኛው ደግሞ በሶማሊያ በስፋት የሚንቀሳቀሰውን ጽንፈኛውን የአል-ሸባብ ቡድንን ለመቀላቀል ሲሞክር የተያዘ ግለሰብ ነው።
እአአ 2015 ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ጽንፈኞች የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥበቃዎችን ገድለው ከገቡ በኋላ በተማሪዎች ላይ ተኩስ ከፍተው በርካቶችን ገድለዋል። የዓይን እማኞች በወቅቱ ክርስቲያን ተማሪዎች ተለይተው በጽንፈኛ ታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግረው ነበር።
የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃትን ያቀነባበረው ሞሐመድ ኩኖ እአአ 2016 ላይ በሶማሊያ ተገድሏል።
ይህ የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃት በኬንያ ታሪክ በሽብር ጥቃት በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ሁለተኛው ጥቃት ነው። እአአ 1998 ላይ አል-ቃይዳ በናይሮቢ በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።












