ሁለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጉምቱ የሕግ ምሁራን መታሰራቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, facebook/the reporter
በኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት እና ጥናት ታዋቂ የሆኑት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራኖቹ ፕሮፌሰር አሰፋ ፍስሐ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቢቢሲ ከተለያዩ ታማኝ ምንጮች አረጋገጠ።
ፕሮፌሰር አሰፋ ፍስሐ በሕገ መንግሥት ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ረዳኢ ደግሞ በአሰሪ እና ሠራተኛ ሕግ ዘርፍ አንቱታን ያተረፉ ምሁር ናቸው።
ፕሮፌሰር አሰፋ በኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ታሪክ ሁለተኛው የሕግ ሙሉ ፕሮፌሰር ናቸው። ከእርሳቸው ቀድሞ ብቸኛው ሙሉ የሕግ ፕሮፌሰር ሆነው የቆዩት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እንደሆኑ ይታወቃል።
ሁለቱም ምሁራን በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል። ተባባሪ ፕሮፌሰር መሐሪ ከቀናት በፊት ለአንድ ቀን ታስራው እንደተፈቱ እና የአሁኑ ሁለተኛ እስራቸው እንደሆነም ምንጮቻችን አክለዋል።
ቢቢሲ ለታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ቅርብ ከሆኑ ነገር ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ ሰዎች ሁለቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን በቁጥጥር ሰር መዋላቸውን አረጋግጠዋል።
ቢቢሲ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ዲን ወደ ሆኑት ብሩክ ኃይሌ (ዶ/ር) በመደወል ስላሉበት ሁኔታ ያውቁ እንደሆነ ጠይቋቆ "ገና ከእናንተ መስማቴ ነው። እስካሁን የማውቀው ነገር የለም" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
በቀጣይ ስለ ምሁራኖቹ ሁኔታ ያጣሩ እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም "በዚህ ደረጃ ይሄ ነው ማለት አልችልም። የሚመለከተው አካል ነው እንጂ እኔ ይህንን አላውቅም" ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ታሰሩ በተባሉት ግለሰቦች ጉዳይ ዙሪያ መረጃ እንደሌላቸው እና አጣርተው መልስ እንደሚሰጡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ሰዎች በቁጥጥር ሥር የሚውሉበት ሁኔታ እና የእስረኞች አያያዝ አፋጣኝ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ከሰሞኑ አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከአዋጁ መደንገግ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ ባይቻለውም በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ 714 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይታሰሩ እንዳልቀሩ ባስታወቀበት መግለጫ በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 300 ሰዎች መታሰራቸውን አስፍሯል።
የተወሰኑ ሰዎች በሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት መረጃ መሰረት የታሰሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ግን ከኅብረተሰቡ ተገኘ በተባለ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር እንደሚውሉና ከታሳሪዎቹም መካከል የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ብዛት ከፍተኛ መሆኑንም ኢሰመኮ ገልጿል።
በተጨማሪም በአንዳንድ ጣቢያ የተያዙ ሰዎች የትግራይ ተወላጅ አለመሆናቸውን በማሳየት ከእስር ሲፈቱም የኢሰመኮ ባለሙያዎች መመልከታቸውን መግለጫው አስፍሯል።
ኮሚሸኑ እድሜያቸው 80 የሚደርስ አረጋውያንን ጨምሮ፣ የሚያጠቡ ሴቶች፣ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው፣ ተከታታይ ሕክምና ያሚያስፈልጋቸው ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው ሰዎች ጭምር በቁጥጥር ስለመዋላቸውን የኢሰመኮ የክትትል ቡድኑ አመልክቷል ይላል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኤጀንሲ ባወጣው ሪፖርት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ቢያንስ አንድ ሺህ ሰዎች በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውን ገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር እንዳሉት "ቢያንስ አንድ ሺህ ሰዎች ባለፈው ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ታስረዋል ተብሎ ይታመናል። አንዳንድ ዘገባዎች አሃዙን በጣም ከፍ አድርገውታል" ብለዋል።












