የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን 'የትግራይ ተወላጆች እስር አሳስቦኛል' አለ

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል

የፎቶው ባለመብት, UN

የምስሉ መግለጫ, የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል

የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት በተለይ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ እስሮች መበራከታቸው አሳስቦኛል አለ።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል በአዲስ አበባ፣ በጎንድር፣ በባሕር ዳር እና በሌሎች ስፍራዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ፖሊስ ፍተሻ እያደረገ እና በርካታ ሰዎችን እያሰረ ነው ብለዋል።

ቃል አቀባይዋ ማክሰኞ ጄኔቭ ላይ በሰጡት መግለጫ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት አብዛኞቹ ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸውም አልያም ደጋፊ ናቸው የሚባሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የሚፈጸሙት እስሮች ብሔርን መሠረት ባደረገ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑ አሳስቦኛል ማለቱ ይታወሳል።

ኢሰመኮ በተለይም በአዲስ አበባ "ማንነትን/ብሔርን መሠረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ መከናወኑ እጅግ ያሳስበኛል" ብሎ ነበር።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ በመዲናዋ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ የሚገኙ "ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ አይደለም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የፖሊስ ቃለ አቀባይ የታሰሩት አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ቢያረጋግጡም የሌላ ብሔር ተወላጆችም መታሰራቸውን ገልጸዋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል በመግለጫቸው ባለፈው ሳምንት ከ1ሺህ ያላነሱ ሰዎች መታሰራቸውን ሪፖርቶች መጠቆማቸውን እና ቁጥሩ ከዚህም በላይ ከፍ ያለ መሆኑን ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።

ሰዎች ታስረው የሚገኙባቸው ቦታዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ደረጃን ባላሟላ በተጨናቀቁ ፖሊስ ጣቢያዎች መሆኑን ቃል አባይዋ ገልጸዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ለምን እንደተያዙ እንዳልተነገራቸው፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን እና ክስ እንዳልተመሰረተባቸው የሚገልጹ አሳሳቢ ሪፖርቶች አሉ ብለዋል።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ እና ሙሉ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ ጠይቀዋል።

ቃል አቀባይዋ አሁንም 10 የተመድ ሠራተኞች እና 34 ከተመድ ውል የያዙ አሸከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አስታውሰው፤ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ እንዲለቀቁ አልያም ደግሞ ገለልተኛ የፍትሕ አካል ሰዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉበትን ምክንያት እንዲመረምሩ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።

ከሳምንታት በፊት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ መሆኑ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሰብዓዊ አቅርቦት የበለጠ ያወሳስበዋል ያሉት ቃል አቀባይዋ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚው አካል ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዲያውል እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ሰዎችን አስሮ የማቆየት ስልጣን ይሰጠዋል አሳስበዋል።

ቃል አቀባይዋ፤ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ኢትዮጵያ ያወጀችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ሁኔታዎችን ከማረጋገት ይልቅ ይዞት የሚመጣው አደጋ ይበልጣል ስለማለታቸው አስታውሰዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወደጅ፤ "የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የበለጠ ያወሳስባል፣ ልዩነቶችን ያሰፋል፣ ሲቪል ማኅበራትን አደጋ ላይ ይጥላል እንዲሁም የሰዎችን ስቃይ ይጨምራል" ብለዋል።

መንግሥት የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ ከተሞችን ተቆጣጥረው መዲናዋን የመያዝ ፍላጎት እንዳላቸው ከተገለጹ በኋላ በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጀው "በአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ በመደቀኑ" ይህንንም አደጋ "በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መቆጣጠር ባለመቻሉ የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን እንዲሁም ዜጎችን በማቀናጀት የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ" ሕጋዊ ማዕቀፍ በማስፈለጉ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል።