ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የተመድ አሽከርካሪዎች መካከል ግማሾቹ ተፈቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ መኪና አሽከርካሪዎች መካከል ግማሾቹ መለቀቃቸውን የድርጅቱ ዋና ቃል አቀባይ ገለጹ።
በኒውዮርክ በተሰጠ መግለጫ ላይ ቃል አቀባዩ ፋርሃን ሃቅ እንደተናገሩት ሰኞ፣ ኅዳር 6/2014 ዓ.ም፣ ታስረው ከነበሩት መካከል 34ቱ አሽከርካሪዎች ቢፈቱም ሌሎች 36 በእስር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም 72 የከባድ መኪና አሸከርካሪዎች አፋር ክልል ሰመራ ውስጥ ባለፈው ሳምንት አርብ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሮይተስና እና ኤኤፍፒ መዘገባቸው ይታወሳል።
የቀሩት የኮንትራት አሽከርካሪዎች እንዲሁም 10 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ከእስር እንደሚፈቱም ቃለ አቀባዩ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች የታሰሩት የፌደራል መንግሥቱ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገገው አማጺው የትግራይ ተዋጊዎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንደሚዘምቱ መናገራቸውን ተከትሎ ነበር።
ሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ 40 ሚሊየን ዶላር የአደጋ ጊዜ ፈንድ መልቀቁንቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
"ይህ ገንዘብ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ለተጠቁ አካባቢዎች የአደጋ ጊዜ መከላከሎችን ከፍ ለማድረግና በደቡብ ኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ ቀድሞ ምላሽ ለመስጠት ይረዳል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት ታጣቂዎች መካከል ለአንድ ዓመት በዘለቀው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።












