መንግሥት ለጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች ድጋፍ እንዳይደርስ ክልከላ አድርጓል- ሂዩማን ራይትስ ዋች

ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዋች የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የጾታዊ ጥቃት ሰላባ ለሆኑ ሰዎች የሚያስፈልገው መሠረታዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ክልከላ አድርጓል ሲል ወቀሰ።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ የትግራይ ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እድሜያቸው ከ6 አስከ 80 በሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸሙትን ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መዝግቦ ይዟል።

በሌላ በኩል ሌላኛው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የአስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ እና አካላዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ገልጿል።

አምነስቲ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው በከተማዋ ነዋሪ የሆኑና ያናገራቸው 16 ሴቶች በህወሓት አማጺያን የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

line

የሂዩማን ራይትስ ዋች የሴቶች መብት አድቮኬሲ ዳይሬክተር ኒሻ ቫሪአ፤ በትግራይ ጦርነት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የጦርነቱ ተሳታፊዎች መጠነ ሰፊ የሆነ እና ሆነ ተብሎ የተደረጉ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብለዋል።

መንግሥት ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃቶች ሰላባ ለሆኑ ሰዎች አስፈላጊ ህክምና እና የአእምሮ ጤና ድጋፍ እንዳያገኙ እክል ሆኗል ብለዋል ዳይሬክተሯ።

የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጀቶች የኢትዮጵያን መንግሥትን እና ህወሓትን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ወሲባዊ ብዝበዛዎችን እንዲያቆሙ፣ አስቸኳይ እና ያልተገደበ እርዳታ በመላው ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲደርስ እንዲሁም የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ምርመራ እንዲደረግባቸው ጫና እንዲያደርጉ ሂዩማን ራይትስ ዋች ጠይቋል።

ድርጅቱ በሪፖርቱ 28 የጤና ባለሙያ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች እና የዓይን እማኞችን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በሪፖርቱ ማካተቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ሚሊሻ በተቆጣጠሯቸው የትግራይ አካባቢዎች አስገድዶ መድፈር፣ ማሰቃየት፣ ግድያ፣ እና ማንነተን መሠረት ያደረጉ ስድቦችን እና የማዋረድ ተግባራትን ስለመፈጸማቸው ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።

የትግራይ ተዋጊዎች ደግሞ በክልሉ በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እንዲሁም በአማራ ክልል በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እና ግድያ ስለመፈጸማቸው ተመልክቷል ብሏል።

"አንድ ቀን የኢትዮጵያ ወታደሮች አንዲት [ታዳጊ] ሴትን ይዘው ወደ ሆስፒታል መጡ። ስንመረምራት ነፍሰ ጡር መሆኗን አረጋገጥን። ገርባ ጊባ የወታደ የወታደር ካምፕ [መቀለ አቅራቢያ የሚገኝ] ውስጥ በወሲብ ብዝበዛ ውስጥ ከቆዩት መካከል አንዷ ነች" በማለት አንድ በመቀለ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩ ሐኪም ለመብት ተሟጋቹ ተናግረዋል።

ይህ የጤና ባለሙያ በታዳጊዋ ፍቃድ ጽንሱ እንዲቋረጥ መደረጉን ተናግረው ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ገብተው ለሕክምና የሚመጡ በርካታ ሴቶች መኖራቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ አካባቢዎች ጦሩን ካስወጣ በኋላ፤ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕጎችን በተጻረረ መልኩ ወደ ክልሉ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ጥሬ ገንዘብ እና ነዳጅ እንዳይገቡ እክል ፈጥሯል ተብሎ ይከሰሳል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት አስተያየትን ለማካተት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት አመልክቷል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አድርጎ ከትግራይ አካባቢዎች የወጣው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስና እርሶ አድሩ በክረምቱ ወራት በግብርና ሥራው እንዲሰማራ ለማስቻል መሆኑን ገልጾ ነበር።

የፌደራሉ መንግሥት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላም የሰብዓዊ እርዳታ ሲያቀርብ መቆየቱን እና አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት የረድኤት ድርጅቶች ለአማጺያኑ የተለያዩ አቅርቦቶችን እያደረጉ ነው በማለት ቅሬታውን ሲያቀርብ ቆይቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሸን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ በጋራ ያካሄዱትን የምርመራ ውጤት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ሁለቱ አካላት ይፋ ባደረጉት ሪፖርት ላይ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰዋል ያሉ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ጥሰተኞች በሰብዓዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር ሊስተካከሉ ይችላሉ ብሏል።

ኢሰመኮ እና ተመድ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑት አካላት ያለ ፍርድ ሰዎችም መግደላቸውን፣ ማሰቃየታቸውን፣ አስደገድደው መድፈራቸውን እና ስደተኞችን ማፈናቀላቸውን በምርመራቸው አረጋግጠዋል።