የህወሓት አማጺያን በደቡብ ጎንደር ነፋስ መውጫ የመድፈር ጥቃቶች መፈጸማቸውን አምነስቲ አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል የነፋስ መውጫ ከተማ ላይ ጥቃት በፈጸሙበት ጊዜ የመድፈር፣ ዘረፋ እና አካላዊ ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ መፈጸማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ።
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው በከተማዋ ነዋሪ የሆኑና ያናገራቸው 16 ሴቶች በህወሓት አማጺያን የመደፈር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
ሴቶቹ እንዳሉት በህወሓት ኃይሎች መሳሪያ ተደቅኖባቸው እንደተደፈሩ፣ ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው እንዲሁም አካላዊ ጥቃት እና ስድብ እንደደረሰባቸው አመልክተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽ ጨምሮ ካነገራቸው የመድፈር ጥቃት ከተፈጸመባቸው አስራ ስድስት ሴቶች መካከል 14ቱ ጥቃቱ በቡድን እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል። አማጺያኑ በከተማ ባሉ የህክምና ተቋማት ላይ ዝርፊያና ውድመትን አድርሰዋል ብሏል።
ህወሓት በተዋጊዎቹ ተፈጽመዋል ስለተባለው ጥቃት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል በወጣው ሪፖርት ላይ ጥያቄ ያነሳ ሲሆን፣ በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።
ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋ በኋላ የህወሓት አማጺያን ወደተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመግባት ጥቃት በፈጸሙበት ጊዜ ነበር ወደ ንፋስ መውጫ ከተማ የገቡት።
በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ የምትገኘውን የነፋስ መውጫ ከተማን የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረው የቆዩት ከነሐሴ 06 አስከ 15/2013 ዓ.ም ድረስ ለአስር ቀናት ነበር።
አንድ የክልሉ አስተዳደር ባለሥልጣን ለአምነስቲ እንደገለጹት አማጺያኑ በንፋስ መውጫ ከተማ በቆዩባቸው ቀናት ውስጥ ከ70 በላይ ሴቶች የመድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሪፖርት አድርገዋል።
"የመድፈር ጥቃቱ ከደረሰባቸው የሰማናቸው ምስክርነቶች የህወሓት ተዋጊዎችን አጸያፊ ተግባራት፤ ከጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ናቸው። ድርጊቶቹ ከሞራል ወይም ከሰብአዊነት ያፈነገጡ ናቸው" ሲሉ የአምነስቲ ኢንትርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ካላማርድ ተናግረዋል።
ጨምረውም የህወሓት ተዋጊዎች ወሲባዊ እና ፆታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶችን እና የዓለም አቀፍ ሕጎች ጥሰቶችን በሙሉ በማቆም በፈጻሚዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
አምነስቲ ያናገራቸው የአካባቢው የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሠራተኛ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 71 ሴቶች በህወሓት ተዋጊዎች የመድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የገለጹ ሲሆን፣ የፌደራል ፍትህ ሚኒስቴር አሃዙ 73 እንደሆነ ያመለክታል።
ከጥቃቱ የተረፉ ሴቶች ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት እንደተናገሩት ጥቃቱን መፈጸም የተጀመረው የህወሓት ኃይሎች ከተማዋን በተቆጣጠሩበት ዕለት ነው።
ሁሉም ሴቶች የመድፈር ጥቃቱ ፈጻሚዎቹን ህወሓቶች መሆናቸውን መለየት የቻሉት በአነጋገር ዘያቸው እና በሚሰነዝሩት ብሔርን መሠረት ባደረገ ስድብ እንዲሁም በግልጽ ህወሓቶች መሆናቸውን በመናገራቸው መሆኑን ገልጸዋል።
አማጺያኑ ከመድፈር ጥቃቱ በተጨማሪ ሰብአዊነትን የሚያጣጥል የብሔር ማንነታቸው ላይ ያነጣጠሩ ስድቦችንና ማዋረድን ይፈጽሙ ነበር። እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ የመድፈር ጥቃቱን የሚፈጽሙት በፌደራል ኃይሎች በትግራይ ሴቶች ላይ የተፈጸመውን ተመሳሳይ ድርጊት ለመበቀል መሆኑን ይናገሩ ነበር ብለዋል።
አምነስቲ ኢንትርናሽናል እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማት ቀደም ሲል የመንግሥት አጋር በሆኑ ኃይሎች እና በሚሊሻዎች ትግራይ ውስጥ ስለተፈጸሙት መጠነ ሰፊ መድፈር እና ፆታዊ ጥቃትን የተመለከቱ መረጃዎችን ማውጣታቸው ይታወሳል።
የህወሓት ታጣቂዎች በነፋስ መውጫ በቆዩባቸው ቀናት ከፈጽሟቸው መድፈር፣ አዋራጅ ንግግር እና አካላዊ ጥቃቶች በተጨማሪ ዘረፋና ንብረት ላይ ውድመትን መፈጸማቸውን የአምነስቲ ሪፖርት አመልክቷል።
የመድፈር ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሴቶች በህወሓት ኃይሎች የተለያዩ ንብረቶቻቸው እንደተዘረፉባቸው ለአምነስቲ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ምግብ፣ ጌጣጌጦች፣ ገንዘብና የሞባይል ስልኮች እንደተወሰደባቸው አመልክተዋል።
አምነስቲ ኢንትርኛሽናል የመድፈርና ሌሎች ጥቃቶች የተፈጸመባቸውን ሴቶችን በተመለከተ ባወጣው በዚህ ሪፖርት ላይ የጥቃቱ ሰለባዎች ያጋጠማቸውን ሰቆቃ ዝርዝር ምስክርነት አካቷል።
የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ያነጋገራቸው 16 የመደፈር ጥቃት ሰለባዎች በድርጊቱ ሳቢያ የተለያዩ አካላዊና አእምሯዊ ችግሮች እንደገጠማቸው ገልጸዋል።
በአካባቢው ያሉ የህክምና ተቋማት በአማጺያኑ በመዘረፋቸውና በመውደማቸው ሴቶቹ የህክምና ድጋፍ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸውም አምነስቲ ገልጿል።
በመንግሥት በአሸባሪ ቡድንነት የተፈረጀው ህወሓት አምነስቲ ኢንትርናሽናል ተዋጊዎቹ ፈጽመውታል ስላላቸው የመድፈር ድርጊቶች፣ ዘረፋ እንዲሁም ሌሎች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን በመተመለከተ ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ በሰጠው ምላሽ ሪፖርቱ ላይ ጥያቄ በማንሳት ተገቢው ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።
የፌደራሉ መንግሥት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ አካባቢዎች ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች በአጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች ጥቃት ከፍተው የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።
በዚህ ሳቢያም የህወሓት አማጺያን የጅምላ ግድያ፣ መድፈር፣ ዘረፋ እና ሌሎች ጥፋቶችን እየፈጸሙ ነው በሚል በተደጋጋሚ ቢከሰሱም ሲያስተባብሉ ቆይተዋል።
የህወሓት ምላሽ
በህወሓት ኃይሎች ላይ በቀረበው ክስ ላይ በትግራይ የውጭ ግንኙነት ጽህፈት ቤት በኩል ረቡዕ ምሽት የወጣን መግለጫ ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋሩ ሲሆን፤ መግለጫው ሪፖርቱ የተዘጋጀበት ዘዴ ላይ ጥያቄ አንስቶ ተዋጊዎቹ ድርጊቱን አይፈጽሙም ሲል ተከላክሏል።
መግለጫው እንዳለው የተጠቀሰው ቦታ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ባለበት ሁኔታ አምነስቲ ስፍራው ድረስ ሄዶ ምርመራውን ከማድረግ ይልቅ ከርቀት ማድረጉ እና የክልል ባለሥልጣናትን በማናገር ያወጣው ሪፖርት ችግር አለበት ሲል ተችቶታል።
በዚህ ሳቢያም ሪፖርቱን ውድቅ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ጠቅሶ ነገር ግን በኃይሎቻቸው ላይ የቀረበውን ክስ በቀላሉ የማይመለከቱት በመሆኑ ጉዳዩን በአግባቡ በመያዝ እንደሚከታተሉት ገልጿል።
ስለዚህም በማንም ይፈጸም በማን በጦርነት ተሳታፊ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርስ የትኛውም አይነት ጾታዊ ጥቃት እና ማሰቃየት በትግራይ ኃይሎች በኩል ተቀባይነት እንደሌለው አመልክቶ፤ ተፈጽሞም ከተገኘ የዚህ አስከፊ ድርጊት ፈጻሚ ለፍርድ እንዲቀርብ ይደረጋል ብሏል።
ነገር ግን ተዋጊዎቻቸው ሥርዓት ያላቸው መሆናቸውንና አላማቸው በትግራይ ውስጥ "ግፍና ሰቆቃን የፈጸሙትን ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ እንጂ ሰላማዊ ሰዎችን ሰለባ ማድረግ አይደለም" በማለት ክሱ በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል ምርመራ እንዲደረግበት ጥሪ አቅርቧል።












