ጄፍሪ ፌልትማን በኬንያ ሁለት ቀናት ቆይተው ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተገለጸ

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ናይሮቢ ኬንያ አቅንተው ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ከመከሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን የአሜሪካ መንግሥት ገለጸ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አምባሳደር ፌልትማን ጥቅምት 28 እና 29/2014 ዓ.ም. በኬንያ ባደረጉት ቆይታ ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከሌሎች የፖለቲካ መሪዎች ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ጉዳይ ተወያይተዋል ብሏል።

ፌልትማን በኬንያ የነበራቸውን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ወደቆዩባት ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው ተነግሯል።

ፌልትማን ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ የገቡት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ላለው ጦርነት አስቸኳይ መፍትሔ ለማፈላግ እንደሆነ ተገልጾ ነበር።

ፌልትማን ጥቅምት 25 እስከ 28 ባሉት ቀናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ከመከላከያ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጋር መወያየታቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ፌልትማን በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው እንደነበረ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የፌልትማንን የጉዞ እንቅስቃሴ ባስታወቀበት መግለጫው አሜሪካ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት መስፋፋት እጅጉን ያሳስባታል ብሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ለተከሰተው ቀውስ መፍትሄ ለመሻት ከዓለም አቀፍ አጋሮች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር መስራቷን ትቀጥላለች ብሏል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ።

ጄፍሪ ፌልትማን በቀጠናው ለተጨማሪ ቀናት እንደሚኖቆዩ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።

ጄፍሪ ፌልትማን በተለይ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ያለውን ጦርነት እና ፖለቲካዊ ቀውስ በቅርበት እንዲከታተሉና በመፍትሔ እንዲያግዙ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት በጆ ባይደን የተሾሙት ከወራት በፊት ነው።

አስካሁንም የፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ በተደጋጋሚ ወደ ቀጠናው አገራት እንዲሁም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተጉዘው የነበረ ቢሆንም ተጨባጭ ውጤት አላገኙም ።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ የተባባሰ ሲሆን፣ በሱዳን ውስጥ ደግሞ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ቀውሱ ወደ ሌላ ደረጃ ተሸጋግሯል።

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ

ግጭቱ በውይይት እንዲፈታ የማደራደር ጥረት

በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ተቀስቅሶ አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማስቆም ምዕራባውያን አገራት እና የአፍሪካ ሕብረት ተዋጊ ኃይሎችን ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ሲወተውቱ ቆይተዋል።

በቅርቡም የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦሉሴንጉን ኦባሳንጆ የፌደራሉ መንግሥት እና የህወሓት መሪዎችን ካነጋገሩ በኋላ፤ "ለማደራደር የማደርገውን ጥረት አልቀበልም ያለ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኦባሳንጆ፤ "የአፍሪካ ሕብረት ሰላም ለማምጣት፣ ንግግርን ለማስጀመር እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ልዩ መልዕክተኛ መሰየሙን ሁሉም ወገን በበጎ ነው የተቀበሉት" ሲሉ ተናግረዋል።

ድርድሩ ምን ላይ እንዳለና በቀጣይ ምን እንደሚፈጠር ጥያቄ የቀረበላቸው ኦባሳንጆ "አሁን ገና የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ነኝ። ድርድሩ ወዴት እንደሚሄድ የምናገርበት ጊዜ አይደለም" ብለዋል።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማርገብ ትናንት በተጠራው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ላለው የሰላም ተነሳሽነት ድጋፉን መስጠቱ ይታወሳል።

የጸጥታው ምክር ቤት ይህን ድጋፍ የሰጠው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር ድርድሩን አስመልክቶ የነበረው ውይይት በበጎ መልኩ ተቀባይነት ማግኘቱን ለምክር ቤቱ ከገለጹ በኋላ ነው።