የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ላለው የሰላም ጥረት ድጋፉን ሰጠ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተውና አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማርገብ በተጠራው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ላለው የሰላም ተነሳሽነት ድጋፍ ተሰጥቷል።
ይህ ድጋፍ የተሰጠው የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር ድርድሩን አስመልክቶ የነበረው ውይይት በበጎ መልኩ ተቀባይነት ማግኘቱን ከገለጹ በኋላ ነው።
በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም በነበረው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባዔ፣ የአባል አገራት ተወካዮች ለሕብረቱ ድጋፍ ከመለገስ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና የትግራይ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ ያልተደናቀፈ ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲደርስና እና አገሪቱን ከቀውስ ለመታደግ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲገኝ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ
"የዕድል መስኮቱ በጣም ጠባብ ነው እና ለማንኛውም ጣልቃ ገብነት ጊዜው አጭር ነው" በማለት በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለምክር ቤቱ 15 አባላት ተናግረዋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉዟቸውን አድርገው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናትና ከትግራይ መሪዎች ጋር የተነጋገሩት ተወካዩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የዓለም አቀፍ መሪዎች ሰላምን ከማስፈን ጋር ተያይዞ የተሰጣቸውን ድጋፍ አስመልክቶ እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት ከተደረገው ጥረት ጋር በተያያዘ ነው ይህንን የተናገሩት።
በትግራይ ኃይሎችና በፌደራል መንግሥቱ የሚደረገው ጦርነት እንዲቆም፣ ውጥረቱን ለማርገብ እና ለውይይት እንዲቀመጡ እንዲሁም ሰላማዊ መፍትሄን ለማበጀት በሚል ተወካዩ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም ተገናኝተዋል። በቅርቡም ወደ ትግራይ ተጉዘው ከመሪዎቹ ጋር ተገናኝተው ውይይት አካሂደዋል።
ከሁለቱም አካላት ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ እንደተናገሩት "ሁሉም መሪዎች ልዩነቶቻቸው ፖለቲካዊ መሆናቸውን ስለሚረዱ ከዚህም ጋር ተያይዞ ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ውይይት አስፈላጊ ነው" ይህም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚረዳበት እድል ይፈጥራል ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ስምንት አገራትን ባቀፈው የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ሕብረት ለመላው ቀጣናው ከፍተኛ ተወካይ ሆኖ ሲሾም ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የመጀመሪያ ናቸው። ከተሾሙም በኋላ በቀጠናው ሰላም፣ መረጋጋት እና ፖለቲካዊ ውይይት ለማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲሁም የዓለም መሪዎችን ድጋፍ ለማግኘት መሞከራቸውን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊን ጨምሮ፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት እና ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተዋል። በተጨማሪም ባለፉት ሳምንታት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ለመግለጽ ሁለት ጊዜ ለፀጥታው ምክር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲያደርጉ እና አፋጣኝ እና አጠቃላይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ የፀጥታው ምክር ቤት ግፊት እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከፍተኛ ልዑኩ የፀጥታው ምክር ቤት ማከናወን አለበት ያሉት ተግባር ለተጎጂዎች ያልተደናቀፈ ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲደርስና ሁሉን ዓቀፍ ውይይቶችና ዕርቀ ሰላም እንዲጀመር ጥሪ ሊያቀርብ ይገባል ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረብም በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን የሰላም ጥረት እንዲደግፍም ጠይቀዋል።
እያሽቆለቆለ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ በማኅበራዊ ኢኮኖሚ መረጋጋት ላይ ተፅእኖ እንዳሳደረ በማየት ቀውሱ እንዳይባባስና አጠቃላይ በቀጣናው ቀጥተኛ ተፅእኖ ስላለለውም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የጋራ እርምጃ እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ
በምክር ቤቱ ኢትዮጵያን የወከሉት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ መንግሥታቸው ባለፈው አንድ ዓመት ከህወሓት የተቃጣበትን ወታደራዊ አደጋ መመከቱን ተናግረዋል። አክለውም መንግሥት ምግብን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅሳቁሶችን በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመተባበር ሲያቀርብ እንደነበር ተናግረዋል።
አምባሳደር ታዬ ለመልሶ ግንባታ ብሎም ለተለያዩ ድጋፎች መንግሥት እስካሁን መቶ ቢሊዮን ብር ያህል ማውጣቱን እንዲሁም ለሰብአዊ ድጋፍ እንዲያመች በሚል የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
"ይህ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል" ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል። "በዚህ የወንጀል ቡድን ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ያስፈልገው የነበረውን አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ እያገኘ አይደለም" ሲሉ አምባሳደር ታዬ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
በአማራ እና በአፋር ክልል በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎችም በየበራቸው ላይ ተገድለዋል ሲሉም አምባሳደር ታዬ ገልጸዋል።
"መንግሥት ወደ ትግራይ ምግብ እና መድኃኒት ጭኖ የላካቸው ተሽከርካሪዎች የጦር መሳሪያዎችን እና ወጣት ተዋጊዎችን እያጓጓዙ ነው። ወጣቶቹ ከወንድሞቻቸው ጋር አንድም የሕዝብ ጥቅም በሌለበት ለጥቂት ስግብግብ ሰዎች ሲባል እንዲዋጉ ተገደዋል" ብለዋል አምባሳደሩ።
አምባሳደሩ "ለፖለቲካዊ ውይይት የሚደረጉ ጥሪዎችን እናከብራለን" ብለዋል። የምዕራባዊያኑ መገናኛ ብዙኃን ብሎም የአንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞች እንዲሁም አመራሮች ለህወሓት በይፋ ድጋፋቸውን ሰጥዋል የሚል ክስም አሰምተዋል።
አምባሳደሩ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል የሚል ሐሰተኛ ሪፖርቶችን ሲወጡ ነበር ብለዋል።
አምባሳደር ታዬ የህወሓት ደጋፊዎች ለቡድኑ የመገናኛ መሳሪያዎችን፣ የሳተላይት መረጃዎችን፣ መሳሪያዎችን እንዲሁም ተዋጊዎችን ከማቅረብ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ችግር ለማገገም ዓለም አቀፍ ድጋፍን እንደምትፈልግም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አገራቸው የአፍሪካ ሕብረት የምሥራቅ አፍሪካ ወኪል ለብሔራዊ ውይይት ያቀረቡትን ሃሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን በተደጋጋሚ ማሳወቋን ጠቅሰዋል።
አህጉራዊ መፍትሄዎች ኢትዮጵያን ለመደገፍ ተመራጭ ናቸው ያሉት ታዬ ወደ ውይይት እንዲሁም ወደ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገው መንገድ ቀጥ ያለ ወይም ቀላል እንደማይሆንም ተናግረዋል።
"በዚህም ምክንያት መንግሥት በአሁን ሰዓት ይህንን የወንጀል ቡድን የማስቆም ሥራ መስራት ላይ ነው ትኩረቱ" ሲሉ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት
በፀጥታው ምክር ቤት የፖለቲካና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሐፊ የሆኑት ሮዝሜሪ ዲካርሎ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት "ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት፣ ከ90 የሚበልጡ የተለያዩ ብሔረሰቦችና 80 ቋንቋዎች ባሉባት አገር ውስጥ ጦርነትና አለመረጋጋት ምን እንደሚያስከትል ማንም ሊተነብይ አይችልም" በማለት ጦርነቱ የደቀነውን አደጋ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ሰፋ የእርስ በርስ ጦርነት ልትገባ የምትችልበት ሁኔታ እውን እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ሪፖርትን በመጥቀስ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ስቃይ ተፈፅሟል ብለዋል።
በቅርቡ የተካሄደውን ብሔራዊ ምርጫም ዋቢ በማድረግ ሕዝቡ ለዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቷል ያሉት ተወካይዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥታቸው እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እና ብሔራዊ ውይይት ለመጀመር ስላለው ፍላጎት መናገራቸውንም አውስተዋል።
ለእንዲህ ዓይነቱ ሁሉን አቀፍ ውይይት በአሁኑ ወቅት ያለው አስፈላጊነት ከመቼውም በላይ ነው ያሉት ኃላፊዋ ኢትዮጵያውያን ጊዜው ከማለፉ በፊት የጋራና የበለፀገ የወደፊት ሕይወት ለመገንባት በአንድነት እንዲሰበሰቡ አሳስበዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ያለውን የአሸማጋይነት ሚናን ደግፈው ህወሓት የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲያቆምና ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩት ስፍራዎችም ኃይሉን እንዲመልስ ጠይቀዋል።
በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ሌላው ያነሱት ጉዳይ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና በኢሰመኮ የጋራ ሪፖርት ላይ የተጠቀሱት ያለ ፍርድ ግድያ፣ ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ በሁሉም አካላት የተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ተዓማኒት ያለው ምርመራ እንዲደረግ ነው።
በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ መባባስ በእጅጉ እንዳሳሳባቸውም የምክር ቤቱ አባላት የገለጹ ሲሆን በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የተጣለው የእርዳታ እገዳም መነሳት እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአየርላንዱ ተወካይ በበኩላቸው ምክር ቤት ለውጥ የማምጣት ኃይል ቢኖረውም ነገር ግን ቀውሱ እየበረታ በመጣበትም ወቅት ሁኔታውን በዝምታ አልፎታል በማለት ወቅሰዋል "ለረጅም ጊዜ በዝምታ ቆይተናል" ሲሉም ተሰምተዋል።
ተዋካይዋ እንደ ኦባሳንጆ ያሉ የአህጉሪቷ መሪዎች እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት መሪን ጨምሮ የቀጣናው ድርጅቶች የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና አስረድተዋል።
ቻይና
ቻይናን የወከሉት ዣንግ ጁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የብሔርና ሌሎች ምክንያቶች ጥምር ውጤት መሆኑን ጠቁመው መፍትሔ የሚገኘው በአገር ውስጥ ብቻ መሆኑን አስምረውበታል።
በአህጉሪቱ ያሉ አገራትና ድርጅቶች ፖለቲካዊ እልባት ለማምጣት ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉም የአገራቸውን አቋም አስረድተዋል።
የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለማግኘት ለሚደረገው ጥረት በድጋሚ ድጋፋቸውን ገልጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ላሳዩትን በጎ ተግባር አመስግነው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ሕብረት ለሚያደርገው ጥረት አስፈላጊውን ጊዜና ቦታ በመስጠት ድጋፍ መለገስ አለበት ብለዋል።
በተለይም አሜሪካና የተለያዩ አገራት የሚያደርጉትን ማዕቀብ በተመለከተም አስተያየታቸውን የሰጡት ተወካዩ፣ በንግድ ላይ ገደብ ማድረግ እና እርዳታን ማቋረጥ በፖለቲካው መፍትሄ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሆነም አስረድተዋል።
ለፀጥታው ምክር ቤት አባላትም ምክራቸውን ያስተላለፉት የቻይናው ተወካይ አባል አገራቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነትና አመራር በማክበር ኢትዮጵያ የሰብአዊ አቅሟን እንድታሻሽል እና የሚሰጠው እርዳታም ሊጨምር ይገባል ብሏል።
በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት፣ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ፣ ሰብአዊ እርዳታን ማመቻቸት እና ሰብአዊ ሁኔታው የከፋ እንዳይሆን ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም
ዩናይትድ ኪንግደምን ወክለው የቀረቡት ጄምስ ካሪዩኪ በቅርቡ በመንግሥት የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን እንደ ሰበብ በመጠቀም የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ ሕጎች ችላ መባል እንደሌለባቸውም አስጠንቅቀዋል።
በተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ መዋሉ፣ እንግልት እና ስቃይ፣ የሰላማዊ ዜጎች ጥቃት እና መፈናቀልን ጨምሮ በርካታ ጥሰቶችን በዝርዝር ጠቅሰው የሰብዓዊ መብት ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት የምርመራ ሪፖርት ውስጥ የተካተቱትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሁሉም ወገኖች ጦርነቱን አቁመው መነጋገር መጀመር እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል። የትግራይ ኃይሎች ግስጋሴያቸውን አቁመው ወደ ትግራይ እንዲመለሱም ጠይቀዋል። የተጣለው የሰብዓዊ እገዳ እንዲነሳ ብሄርን መሰረት ያደረገ ልዩነትና ከጥላቻ ትርክቶች መቆጠብም እንደሚገባ አሳስበዋል።
አሜሪካ
በፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ንግግራቸውን የጀመሩት ባሳላፍነው አርብ ምክር ቤቱ ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ወኪል ጋር እንዲተባበር የያዘውን አቋም በመደገፍ ነው።
ሊንዳ አንድ ዓመት ባስቆጠረው በዚህ ጦርነት ወቅት "ለረጅም ጊዜ በዝምታ ቆይተናል" ብለዋል። በጦርነቱ ወቅት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን የተናገሩት ሊንዳ፣ ይህም መድፈርን እንደ የጦርነት መሳሪያ መጠቀምን ያጠቃለለ ነው ብለዋል።
"ሁሉም ኃሃይሎች ጥፋተኞች ናቸው፤ ጥፋት የለሌለበት የለም" ሲሉ አምባሳደሯ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ለአንድ ወገን ያዳላል በሚል የሚቀርበበት ክስ አግባብ እንዳልሆነ ያጣጣሉት ሊንዳ ተቋሙ ማንኛውንም ጥቃቶችን እንዲሁም በየትኛውም ወግን የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚቃወም ተናግረዋል።
ሊንዳ የህወሓት ተዋጊዎች ጥቃታቸውን ወደ አዲስ አበባ እንዳያሰፉ እና አሁን ከያዟቸው አካባቢዎች በመልቀቅ ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለሱ አሳስበዋል። እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕጎችን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ሕጎችን እንዲያከብር ጠይቀዋል።
"በመጨረሻም ሰላምን ሊያመጡ የሚችሉት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው" ሲሉ አምባሳደሯ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።












