የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እየተባባሰ መሄዱ በጽኑ እንዳሳሰበውና በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ።
አርብ ምሽት ከተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ በኋላ በአስራ አምስቱም አባላቱ ተቀባይነት አግኝቶ በወጣው መግለጫ ላይ ሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ጦርነቱን በማቆም "ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ የተኩስ አቁም ለማድረግ" ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቀርቧል።
መግለጫው አክሎም ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሔ ለማግኘት እንዲቻል እና ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል።
የምክር ቤቱ አባላት ችግሩን ለመፍታት የአፍሪካ ሕብረትን በመሰሉ አካባቢያዊ ድርጅቶች በኩል የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉና የሕብረቱ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ተኩስ እንዲቆምና ጦርነቱ ሰለማዊ መቋጫ እንዲያገኝ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጿል።
ጨምሮም ሁሉም ወገኖች "ከአደገኛ ጥላቻ ከሚያስፋፉ፣ ግጭትንና መከፋፈልን ከሚያነሳሱ ንግግሮች" እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ከቀናት በፊት አንድ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳትን እንዳስከተለ የተለያዩ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ለበርካታ ጊዜያት በጉዳዩ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በተለይ ግጭቱ ባስከተለው ሰብአዊ ቀውስ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ መክሯል።
ትናንት አርብ በፀጥታው ምክር ቤት የተካሄደው ስብሰባ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለው አንድ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲመክር ለ11ኛ ጊዜ ነው።
ሮይተርስ ብዙም ያልተለመደ ያለውን መግለጫ ለማውጣት ምክር ቤቱ ለበርካታ ሰዓታት ሲደራደር መቆየቱንና መጨረሻ ላይ ከሩሲያ ጋር ከሚያስማማ ነጥብ ላይ መደረሱን ዲፕሎማቶች እንደነገሩት ዘግቧል። እንዲህ አይነቱ መግለጫ ከመውጣቱ በፊት ከምክር ቤቱ አባላት ሙሉ ስምምነት ሊያገኝ ይገባል።
በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላቸው ሩሲያና ቻይና ከዚህ ቀደም በተደረጉ የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ነው ሲሉ አቋማቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል። በዚህም ሳቢያ ጠንካራ እምርምጃም ሆነ ማዕቀብ ከፀጥታው ምክር ቤት ሊወጣ እንደማይችል ሮይተርስ ዘግቧል።
የፀጥታው ምክር ቤት በመግለጫው በግጭቶቹ አካባቢዎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ሕጎች እንዲከበሩ፣ የሕዝብ አገለግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እና የሚቀርቡ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች እንዲጠናከሩ ጥሪ አቅርቧል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ውስጥ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጾ፤ ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮኑ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን 400 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ ብሏል።














