"ለማደራደር የማደርገውን ጥረት አልቀበልም ያለ የለም" ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የፌደራል መንግሥቱን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለማደራደር የሚያደርጉትን ጥረት 'አልቀበልም' ያለ ወገን እንደሌለ ለቢቢሲ ገለጹ።

ወደ ትግራይ መዲና መቀለ ሄደው ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገው የተመለሱት ልዩ መልዕክተኛው፤ "ለማደራደር የማደርገውን ጥረት 'አልቀበልም' ያለ የለም" ሲሉ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

ለማሸማገል እየሞከሩ ካሉት የፌደራል መንግሥት ወይም የህወሓት አመራሮች ዘንድ ሸምግልናውን አልቀበልም ያለ ወገን አለ? ተብለው የተጠየቁት ኦባሳንጆ፤ "የአፍሪካ ሕብረት ሰላም ለማምጣት፣ ንግግርን ለማስጀመር እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ልዩ መልዕክተኛ መሰየሙን ሁሉም ወገን በበጎ ነው የተቀበሉት" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ "የጠየቅኩትን ትኩረት ሰጥተውኛል። በሚገባው ልክ አስተናግደውኛል" ሲሉ ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ገልጸዋል።

አያይዘውም "ትግራይ ስገባም የትግራይ ፕሬዝዳንት አየር ማረፊያው ድረስ መጥተው ተቀብለውኛል። ሌላ የአፍሪካ መሪ በሚቀበለኝ ክብር ነው የተቀበሉኝ" ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛው ኦባሳንጆን "አልተቀበሉንም የሚለው ሐሳብ ፍጹም ስህተት ነው" ሲሉም አክለዋል።

ድርድሩ ምን ላይ እንዳለና በቀጣይ ምን እንደሚፈጠር ጥያቄ የቀረበላቸው ኦባሳንጆ "አሁን ገና የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ነኝ። ድርድሩ ወዴት እንደሚሄድ የምናገርበት ጊዜ አይደለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አሁን ያሉበት ደረጃ በተደራዳሪ ወገኖች ዘንድ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ምን እንደሆነ የመለየት እንደሆነም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኦባሳንጆ "ይዘው የሚመጡትን መፍትሔ እየጠበቅኩ ነው" ሲል ገልጿል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ የአፍሪካ ቀንድ ልዑኩ "ከትግራይ ፕሬዝዳንት ከደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል። በወቅታዊው የኢትዮጵያ ቀውስ ዙርያ የትግራይ አቋም ምን እንደሆነ ገልጸውላቸዋል" ሲሉ በይፋዊ ትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

ኦባሳንጆ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በሁለቱም ወገን በኩል የእሳቸው የማደራደር ጥረት ተቀባይነት አግኝቷል።

"ማንም የእኔን የማደራደር ሐሳብ ውድቅ አላደረገም። ሁሉም ያሉት እርስዎ ለማደራደር መመረጥዎን እናከብራለን ነው። እንደ እርስዎ ሐቀኛ አሸማጋይ ስንፈልግ ነው የነበረው። ከእርስዎ የተሻለ አሸማጋይ አናገኝም ብለዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኦባሳንጆን በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛነት ሲሾም የመጀመሪያ ጉዳያቸው አድርገው የወሰዱት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ነው።

እሳቸው እንዳሉት፤ ኃላፊነቱ ሲሰጣቸው መጀመሪያ ያደረጉት ነገር በአፍሪካ ቀንድ እና ከአፍሪካ ቀንድ ውጪ ያሉ ባለድርሻ አካላትንም ማማከር ነው።

ከዚያም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላትን እንዳገኙ ጠቅሰው፤ "ሁሉም የሚያሳስባቸውን ነገር እንዲሁም ፍላጎታቸውን ገልጸዋል" ሲሉ አሁን የሚገኙበትን ደረጃ ገልጸዋል።

ህወት ስለ ውይይቱ ምን አለ?

ውይይቱን አስመልክቶም የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ፎከስ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለመጀመሪያ ጊዜ የትግራይ አመራሮችን ከማግኘታቸው አንፃር በርካታ ጥያቄዎች ነበሯቸው ብለዋል።

ከትግራይ በኩል ያለውን ጉዳይ እንደሰሙና በኦባሳንጆና በትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል መካከል የተደረገውም ውይይት ሁኔታዎችን ግልፅ ለማድረግ እንደሚረዳም አቶ ጌታቸው አስረድተዋል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ጊዜው ገና ነው ካሉ በኋላ ሁለቱም አመራሮች በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ቀውስ ለማቆም መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችም የየራሳቸውን ምክረ ሐሳብ መጥቀሳቸውን በማንሳት አቶ ጌታቸው ጠቅለል ባለ ሁኔታ ገልጸዋል።

"እኛ የትግራይ ተወላጆች በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ በጽኑ ይሰማናል። እናም ፕሬዚዳንት ደብረጽዮን እድሉን ተጠቅመው የግጭቱን አፈታት በተመለከተ ከትግራይ በኩል ያለውን አቋም በሰፊው አስረድተዋል" ብለዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ከሆነ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የቆመው ብቸኛው እንቅፋት "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፖለቲካዊ ችግርን በወታደራዊ የመፍታት አባዜ ነው" ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ ምርጫ በማድረጉና የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብቱን በቁም ነገር በመያዝ ጫና እንደተደረገበት ጠቅሰው "ሰዎች የመምረጥ መብታቸውን በመጠቀማቸውም ጦርነት ታውጆባቸዋል" ብለዋል።

"አንድ መሪ የመምረጥ መብታቸውን በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ ጦርነት ሲከፍት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው" ብለዋል አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ።

አሁን ወዳለው ጉዳይ ብንመጣና የፌደራል መንግሥት ወታደራዊ መንገዶችን ብቻ እየተጠቀመ ነው ይላሉ? እናንተስ ኃይሎቻችሁ ከኦሮሞ ነፃነት ጦር ጋር ተጣምሮ የለም። ወደ አዲስ አባባ እየገሰገሳችሁ ባላችሁበት ወቅት አላማችሁስ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ለአቶ ጌታቸው ከቢቢሲ ቀርቦላቸዋል።

የትግራይ ኃይል የፌደራሉን ጦር ከአብዛኛው የትግራይ ክፍል ካስወጣ በኋላ አሁንም ጠላት ብለው በጠሯቸው ኃይሎች ግዛቶቻቸው እንደተያዘና ሙሉ በሙሉ ነፃ እንዳልወጣ ይናገራሉ።

የፌደራሉ ጦር ከትግራይ ከወጣም በኋላም የጠበቁት ነገር ቢኖር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመሰረቱ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይስማማሉ የሚል ነበር ብለዋል።

"እየተዋጋን ያለነው በትግራይ ሕዝብ ላይ በታንክና በመድፍ ያልተሳካላቸው በመክበብ ለማሳከት በሞከራቸው ነው። አብይ ከጫነብን ማነቆ ህዝባችንን ማዳን ነበረብን። የዐቢይ ማነቆ እስከቀጠለ ድረስ ሕዝባችንን በረሃብ ለማንበርከክ እስከቀጠለ ድረስ ልጆቻችን ባለው ሁኔታ መሞታቸውን ከቀጠሉ እኛ ተገቢ እርምጃዎችን መውሰድ እንቀጥላለን" በማለት አስረድተዋል።

እገዳው ካልተነሳ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት በረሃብ አፋፍ ላይ ላሉት ሚሊዮኖች እርዳታ እስካልደረሰ ድረስ ዘመቻው ወደ አዲስ አበባ ይቀጥላል ነው እያሉ ያሉት በማለት ቢቢሲ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር።

አቶ ጌታቸው እግዱ እስካልተነሳ ድረስ ዘመቻው አዲስ አበባም ሆነ የትም ቦታ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ዋናው አላማቸው ግን አዲስ አበባ መድረስ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

"የአዲስ አበባን ሕዝብ የማሸበር ሥራ ላይ አይደለንም። እኛ እያደረግን ያለነው ከዚያ የሚመጣን አደጋ የማስወገድ ሥራ ነው። እናም እንደ እኔ መንግሥት የሚያደርገውን ሁሉ ኃላፊነት የሚሰማው አካል እናደርጋለን። ጦርነቱን የጀመረው ዐቢይ ነው እና ዐቢይ በእኛ ጥያቄ ተስማምቶ ግጭቱን ማስቆም የሚችለውም እሱ ነው"ብለዋል።

የሰሜኑ ጦርነት በተለይም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እጅግ እየተባባሰ መጥቷል። ይህን ተከትሎም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ሁለት ቀናት መቆየታቸው ይታወሳል።

ከኦባሳንጆ በተጨማሪ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ኃላፊ የሆኑት ማርቲን ግሪፊትስም ወደ ተጉዘው እንደነበር ተገልጿል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የተፋፋመውን ጦርነት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለ12ኛ ጊዜ ውይይት አድርጓል።

ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት የሞላው ጦርነት ከወራት በፊት ወደ አማራና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አሁንም እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በድርድር መፍትሄ እንዲፈለግለት የተለያዩ አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም አስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይታይ እንደቀጠለ ይገኛል።

በዚህ ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገምታሉ።

የተባሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ።