የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬም በኢትዮጵያ ጉዳይ ይወያያል

የፎቶው ባለመብት, UN
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ይወያያል ተባለ።
የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ዓርብ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተወያይቶ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እየተባባሰ መሄዱ በጽኑ እንዳሳሰበውና በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ዓርብ ምሽት ከተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ በኋላ በአስራ አምስቱም አባላቱ ተቀባይነት አግኝቶ በወጣው መግለጫ ላይ ሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ጦርነቱን በማቆም "ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ የተኩስ አቁም ለማድረግ" ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቀርቦ ነበር።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመክረው የህወሓት አማጺያን የሰሜን እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን ተቆጣጠረው፤ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባን የመያዝ ፍላጎት እንዳላቸው በገለጹበት እና የአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም የሰብአዊ ጉዳዮች ተወካዮች ወደ መቀለ ተጉዘው ከህወሓት ሊቀመንበር ጋር ከተገናኙ በኋላ ነው።
ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ ተደጋጋሚ ውይይቶችን ማካሄዱ ይታወሳል። ዛሬ የሚካሄደው ስብሰባም ለ12ኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።
ምክር ቤቱ ዛሬ "ሰላም እና ፀጥታ በአፍሪካ" በሚለው አጀንዳ ስር የሚወያይ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል።
የዛሬው ስብሰባ እንዲካሄድ የተጠየቀው በሜክሲኮ፣ አየርላንድ፥ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ቱኒዚያ እና ሴንት ቪንሰንት እንዲሁም ግራኒዲስ ነው።
የፀጥታው ምክር ቤት ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ለበርካታ ጊዜያት በጉዳዩ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በተለይ ግጭቱ ባስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ መክሯል።
በፀጥታው ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላቸው ሩሲያና ቻይና ከዚህ ቀደም በተደረጉ የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት የአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ነው ሲሉ አቋማቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመቱን ያስቆጠረ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳትን እንዳስከተለ የተለያዩ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጾ፤ ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮኑ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን 400 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ ብሏል።












