የፀጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና መሰጠት ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, EBC
የ2013 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የፀጥታ ችግር ከሌለባቸው አካባቢዎች ውጪ በቀሩት አካባቢዎች መሰጠት ጀመረ።
በ2013 የትምህርት ዘመን ከ617 ሺህ በላይ ተፈታኞች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናውን ለመውሰድ የተመዘገቡ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት የተፈታኞች ቁጥር በእጥፍ እንደሚበልጥ ተገልጿል።
የአገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ እንዳስታወቁት ተማሪዎች ፈተናውን ከሁለት ሺህ በሚበልጡ የፈተና ጣቢያዎች ለመፈተን ተመዝግበዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በሁለት ዙር ፈተናው እንደሚሰጥ ገልጸው ከ90 በመቶ በላይ ተፈታኞች በመጀመሪያው ዙር ፈተናቸውን እንደሚወስዱም አመልክተዋል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በቀጣይ ሁለተኛው ዙር ፈተና ይሰጣል ብለዋል።
ሁለተኛው ዙር ፈተናም በደቡብ ወሎ፣ ሠሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች እንደሚሰጥ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በአጠቃላይ በአማራ ክልል ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎች ፈተናውን አይወስዱም ተብሏል።
ኃላፊው አክለውም በሁለተኛው ዙር ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የሥነልቦና ግንባታና የትምህርት ክለሣ በመስጠት ለፈተና እንዲዘጋጁ ይደረጋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎች በ62 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን ይወስዳሉ።
የትምህርት ሚንስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በከተማው በሚገኙ ጣቢያዎች ዛሬ የተጀመረውን የፈተናውን ሂደት ጎብኝተዋል።













