የአፍሪካ ሕብረቱ ተወካይ ኦባሳንጆ ዛሬ ወደ ባሕር ዳር እና ሰመራ ይጓዛሉ

በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ሕብረት ከፍተኛ ወኪል የሆኑት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ዛሬ ወደ አፋር እና አማራ ክልል በማቅናት ከክልሎቹ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ።
ኦባሳንጆ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ሁለቱ ክልሎች ለተስፋፋው ጦርነት መፍትሄ እንዲፈላልጉ በአፍሪካ ሕብረት የተሰየሙ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣንት እንዲሁም ባለፈው ሳምንት መብቂያ ላይ ከትግራይ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።
መልዕክተኛው በአሁኑ ወቅት ዋነኛው ጦርነት እየተካሄደባቸው ያሉትን የአማራ እና የአፋር ክልሎችን ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 30/2014 ዓ.ም ወደ ባሕርዳር እና ሰመራ በማቅናት ሲጎበኙ ከክልሎቹ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር እያደረጉት ስላለው የሰላም ጥረት ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኦባሳንጆ ዛሬ ስለሚያደርጉት ጉዞ ለፀጥታው ምክር ቤት የተናገሩ ቢሆንም ስለጉዟቸው የተናገሩት ዝርዝር ነገር የለም።
ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ አንድ ዓመት የሞላውን ጦርነት ለማስቆም እያደረጉት ባለው ጥረት ከሁሉም ወገኖች በኩል ተቀባይነት ማግኘታቸውን ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እየተባባሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ በአስቸኳይ ማስቆም እንደሚያስፈልግ ትናንት ምሽት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት የተናገሩት የሕብረቱ መልዕክተኛ ኦባሳንጆ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ጋር በቅድሚያ ተነጋግረዋል።
ባለፈው ዕሁድ ደግሞ ወደ መቀለ አቅንተው የህወሓት ሊቀመንበር እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር ተወያይተዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ሆነው የተሰየሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ አስካሁን ባደረጉት ውይይት ከሁሉም ወገን በአውንታዊ ሁኔታ አቀባበል እንዳገኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እያደረጉት ስላለው ጥረት ሰኞ ዕለት ያስረዱት ኦባሳንጆ በአስቸኳይ አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንዲደረግ በማሳሰብ፣ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ተደርጎ ያለገደብ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስ ጠይቀዋል።
ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት የሞላው ጦርነት ከወራት በፊት የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ወደ ሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አሁንም እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በድርድር መፍትሄ እንዲፈለግለት የተለያዩ አገራት፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም አስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይታይ እንደቀጠለ ይገኛል።
በዚህ ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገምታሉ።
የተባሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ።












