ከ92 ሺህ በላይ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ይዘቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በስድስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ከ92 ሺህ በላይ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ይዘቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ሜታ [ፌስቡክ] ገለጸ።

እርምጃው የተወሰደው የድርጅቱን የጥላቻ ንግግርን ደንብን በጣሱት ላይ መሆኑን እና 98 በመቶ ያህሉ በሌሎች ሪፖርት ከመደረጉ በፊት እንደተደረሰባቸው ጠቅሷል።

ዓለም አቀፉ ማኅህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ መከታተል የጀመረው አሁን ሊሆን ቢችልም ሜታ ግን "ከሁለት ዓመታት በላይ በአገሪቱ ውስጥ ከነበሩት አስከፊ የግጭት ስጋቶች አንጻር የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አጠቃላይ ስትራቴጂን በመተግበር ላይ ቆይተናል" ብሏል።

በዚህም ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን "ለግጭት እና ለአመጽ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው ብለን ወደምናምንባቸው አገራት ምድብ አሸጋገረናታል" ብሏል።

ደርጅቱ የተቋሙን ፖሊሲዎች የሚጥሱ ይዘቶችን በማስወገድ፣ የሰዎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በመደገፍ እና ሰዎች ኦንላይንም ሆኑ አልሆኑ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ትኩረት አድርጎ መስራቱን አክሏል።

በአገሪቱ ውስጥ ብዛት ያላቸው ቋንቋዎች ስለሚገነሩ በሁሉም መስክ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ያሰበውን በሙሉ ማሳካት አዳጋች መሆኑንም ጠቁሟል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የሪፖርት ማቅረቢያ እና የማስፈጸሚያ ዘዴዎችን በእጅጉ ማሻሻሉንም አስታውቋል።

ለግጭቱ ማዕከል በሆኑት እና በአራቱ ዋና ዋና ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማሊኛ እና በትግርኛ የሚወጡ ይዘቶችን መገምገም ችለናል ብሏል።

ኢትዮጵያውያን፣ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ጥሰቶችን ሲያዩ በቀላሉ የሚያሳውቁበትን ዘዴ ከማመቻቸት ባለፈ የተፈጸሙ ጥሰቶች መመርመር እንችላለንም ብሏል።

በአማርኛም ሆነ በአፋን ኦሮሞ የሚነገሩ የጥላቻ ንግግሮችን ማንም ሳያሳውቃቸው በፊት የምንለይበት ቴክኖሎጂ ባለቤቶች መሆናቸውንም ጠቅሷል።

በዚህም ምክንያት ከግንቦት እስከ ጥቅምት 2021 ባለው ጊዜ የድርጅቱን ፖሊሲ በመጻረር የጥላቻ ንግግር ይዘት ያላቸውን ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ከ92,000 በላይ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ይዘቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

ግንቦት 2021 የተቃዋሚ ፖለቲከኞች/ቡድኖችን በአማርኛ የሚያብጠለጥሉ ሐሰተኛ ገጾችን ማስዱን ጨምሮ ጠቅሷል።

"ከእነዚህ ጽሁፎች ጀርባ ያሉ ሰዎች የተቀናጀ እና ትክክለኛ ያልሆነ መለያ በመጠቀም ሰዎች ማን እንደነበሩ እና ምን እየሠሩ እንደሆነ የማሳሳት ጥረት አድርገዋል" ብሏል።

መጋቢት 2021ም በተመሳሳይ ግብፅ ሆነው ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ቱርክ ላይ ያነጣጠሩ ገጾችን ማገዱን አስታውቋል።

በሚያስተዳድራቸው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚወጡ ይዘቶችን ለመቆጣጠርና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን አሰራሩን ማጠናከሩን የሚናገረው ሜታ በኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩሩ ይዘቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አሳውቋል።

በቅርቡም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ በገጻቸው ላይ ያወጡት ጽሁፍ "ግጭት ቀስቃሽ ነው" ሲል እንዲነሳ ማድረጉ ይታወሳል።

ፌስቡክ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ኢትዮጵያውያን ጥቅም ላይ የሚውል የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ለሚከሰቱ የጥላቻ እና ቀግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ማስተላለፊያነት ውሏል በሚል ይወቀሳል።

የቀድሞ የድርጅቱ ሠራተኞ የነበረችው ፍራንሲስ ሐውገን በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርባ ፌስቡክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ሐሰተኛ መረጃ እና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለማስቆም እንዳልቻለ ተናግራለች።

ከተለያዩ ወገኖች ጠንካራ ትችት የሚቀርብበት ፌስቡክን የቀድሞ ሠራተኛው ፍራንሲስ ሐውገን ባጋለጠችው ምስጢር በኢትዮጵያ እና በምያንማር ግጭት ቀስቃሽ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ሳያስቆም ቀርቷል ብላለች።

"እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ አሁን ላይ የምናያቸው ጽንፈኛ ድርጊቶች እየተባባሱ ይሄዳሉ ብዬ እፈራለሁ። በኢትዮጵያ እና በምያንማር ያየናቸው ነገሮች ወደባሰ ደረጃ የሚደርሱ፣ የአስፈሪ ታሪክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ናቸው" ብላ ነበር።