በከሚሴ ምን ተከሰተ፣ አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች?

ከሚሴ

የህወሓት አማጺያን እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን መዲና የሆነችውን ከሚሴን መቆጣጠራቸውን ከቀናት በፊት ካስታወቁ በኋላ የዞኑ አስተዳዳሪ አማጺያኑ 'ከተማዋን በቁጥጥር ሥር አውለዋል ማለት አይቻልም' አሉ።

የህወሓት አማጺያን ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም በቴ፣ ቡርቃ እና ሐርቡን መቆጣጠራቸውን ገልጸው ጥቅምት 24 ደግሞ መንግሥት ሸኔ ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር በመሆን የከሚሴ ከተማን ተቆጣጥረተናል ማለታቸው ይታወሳል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አሕመድ ሐሰን ግን "ይህ ሐሰት ነው" ይላሉ። የዞኑ አስተዳዳሪ "ተቆጣጠረዋል ሳይሆን ወደ ከተማ ገብተዋል። በተረጋጋ ሁኔታ ግን ከተማዋን አልተቆጣጠሩም። ተኩስ ነው የሚሰማው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዞኑ ነዋሪ ደግሞ በዞኑ የመንግሥት መዋቅር አለመኖሩን እና አካባቢው በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር እንዳለ ይናገራሉ።

የአየር ጥቃት

አማጺያኑ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን መዲና ከሚሴን መቆጣጠራቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ በከሚሴ እና አካባቢዋ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ስለመገደላቸው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ካለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 27 ጀምሮ ጨፋ ሮቢት እና በቴ በሚባሉ አካባቢዎች እንዲሁም የአጣዬ ገጠራማ ቦታዎችን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ቢያንስ 33 መገደላቸው አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ነዋሪ በአየር ጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ በርካታ ቤቶች ሲቃጠሉ ማየታቸውን ተናግረዋል።

በቴ ተብሎ በሚጠራ ገጠራማ ስፍራ አሁንም ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን እና በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ያለ ሰብዓዊ እርዳታ በተለያዩ ቦታ ተበታትነው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የጂሌ ዱሙጋ ወረዳ ሰንበቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ደግሞ፤ ምንም እንኳ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ጦርነት ባይኖርም አጣዬ ከተማ አካባቢ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን እና የከባደ መሳሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ይናገራሉ።

እኒህ ነዋሪ ከቀናት በፊት በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ጨፋ ሮቢ ከተማ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን አውቃለሁ ይላሉ።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ሐሰን ግን እየተካሄደ ባለው ውጊያ በአየር ጥቃት የተጎዳ ንጹሃን ዜጎች የሉም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፌደራሉ መንግሥቱ በቅርብ ሳምንታት በህወሓት አማጺያን ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የአየር ጥቃት ሲያስታውቅ የቆየ ሲሆን፣ እስካሁን ግን በከሚሴ እና በከሚሴ ዙሪያ ስለተደረገ የአየር ጥቃት ያለው ነገር የለም።

በዞኑ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ውጊያ "ሰዎች ተገድለዋል፣ ዘረፋ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሟል" ያሉት አቶ አሕመድ ሐሰን፤ አርጡማ ፉርሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን እና በተቀረው ቦታ ግን አርሶ አደሩ "አራትም፤ አምስትም ሆኖ አማጺያኑን እየተዋጋ ይገኛል" ብለዋል።

አስተዳዳሪው ጨምረውም የህወሓት አማጺያን ወደ ዞኑን የተለያዩ አካባቢዎች "ገብተዋል" ካሉ በኋላ፤ "በተረጋጋ መልክ ግን አልተቆጣጠሩም። ተኩስ ነው የሚሰማው" ብለዋል።

"የወያኔ አጋር የሆነው ሸኔ ነው በኦሮሞ ስም ከእነሱ [ከህወሓት አማጺያን] ጋር እየተዋጋ ያለው" በማለት ተናግረዋል።

ሌላ የሰንበቴ ከተማ ነዋሪው የሆኑ ግልሰብ ሰንበቴ አካባቢ ውጊያ አለመኖሩን ገልጸው፤ ከአጣዬ አቅጣጫ ግን ከባድ የጦር መሳሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ይናገራሉ። ነዋሪው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰንበቴ ከተማን እያቋረጠ ወደ አጣዬ አቅጣጫ ሲጓዝ እየተመለከትን ነው ይላሉ።

"የተፈናቀለ ሕዝብ የለም"

የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አሕመድ ሐሰን በዞኑ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከቀዬው የተፈናቀለ ነዋሪ የለም ይላሉ።

"ሕዝባችን አይፈናቀለም። መሬቱን ለመውረር የመጣውን ተዋግቶ ይመክታል እንጂ መሬቱን ጥሎ አይፈናቀለም። ሕዝባችን መሬቱ ላይ ሆኖ ሊንደው፣ ሊዘረፈው፣ አስገድዶ ሊደፍር እና ኦሮሞን ሊሰብር፣ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የመጣውን ኃይል እየተዋጋ ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

አስተዳደሪው በንጹሃን የዞኑ ነዋሪዎች ላይ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ዘረፋዎች በአማጺያኑ መፈጸማቸውን ጨምረው ተናግረዋል።