ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩ የተመድ ሠራተኞች እንዲፈቱ ጠየቁ

አንቶኒኦ ጉተሬዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሰራቸው የድርጅቱ ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ አቀረቡ።

የጉቴሬዝ ቃል አቀባይ ዋና ፀሐፊው እስከሚያውቁት ድረስ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የተመድ ሠራተኞች ላይ ክስ አልተመሰረተም፤ በምን ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉም አልተገለጸላቸውም ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ መኪና አሽከርካሪዎች መካከል ግማሾቹ መለቀቃቸውን ተመድ ማስታወቁ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ታስረው ከነበሩት 72 ከድርጀቱ ጋር ከሚሰሩ አሸከርካሪዎች መካከል 34ቱ ቢፈቱም ሌሎች 36 በእስር ላይ እንደሚገኙ የተመድ ቃል አቀባይ አስረድተው ነበር።

ከአሸከርካሪዎቹ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን የሆኑ 10 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች በእስር ላይ ይገኛሉ።

ጉቴሬዝ የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ ወሳኝ እና ገለልተና ሥራዎችን እንደሚያከናውን አስታውስው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በተመድ ሠራተኞች ላይ እስር እንዳይፈጽም ጠይቀዋል።

ዋና ፀሐፊው፤ የአገሪቱ ባለስልጣናት ብሔርን መሠረት ያደረጉ እስረኞችን በይፋ እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ግን ሰዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ የሚገኙት "ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ አይደለም" ይላሉ።

"ወታደራዊው ግጭት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት አያመጣም" ያሉት ዋና ጸሐፊው፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ግጭት አቁመው ልዩነቶችን በንግግር እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ደኅንነቱ የተረጋገጠ እና ክልከላ ያልተደረገበት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በአስቸኳይ መመለስ አለበት ያሉት ጉቴሬዝ፤ "ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና ሊፈታ የሚችለው ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን በሚያሳትፍ ውይይት ነው" ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት በመላ አገሪቱ ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ የመንግሥት ፀጥታ አካላት በርካቶችን በቁጥጥር ሥር እያዋሉ ይገኛሉ።

ይህን ተከትሎ ትናንት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት በተለይ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ እስሮች መበራከታቸው አሳስቦኛል ብሎ ነበር።

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል ትናንት ባወጡት መግለጫ በአዲስ አበባ፣ በጎንድር፣ በባሕር ዳር እና በሌሎች ስፍራዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ፖሊስ ፍተሻ እያደረገ እና ከ1ሺህ ያላነሱ ሰዎችን ስለማሰሩ ገልጸዋል።