አሜሪካ ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ዳግም አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa Press Secretary/FB
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ ያሉ ዜጎቹ በአስቸኳይ ከአገሪቱ እንዲወጡ ዳግም ማሳሰቡን ሮይተርስ ዘገበ።
አሜሪካ ዜጎቿን በአስቸጋሪ ጊዜ ከኢትዮጵያ ለማውጣት ወታደራዊም ይሁን የንግድ አውሮፕላኖችን የመጠቀም ዕቅድ እንደሌላት ሮይተርስ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊን ጠቅሶ ዘግቧል።
በተመሳሳይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ተመሳሳያ ማሳሰቢያ መስጠታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ አል አረቢያ ዘግቧል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቹ እንዲወጡ ማሳሰቡ ይታወሳል።
ከአሜሪካ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እና ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ለማድረግ የጉዞ ዕቅድ ካላቸው በአንክሮ እንዲመረምሩ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ከእነዚህም አገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሩሲያ ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አገራት ያስለላለፉት ማሳሰቢያ የተጋነነ ነው ሲል አጣጥሎታል።
አገራቱ ባወጡት የጉዞ ማስጠንቀቂያ ላይ ወደፊት ከኢትዮጵያ መውጣት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ዜጎቻቸው የንግድ በረራ አማራጮች እስካሉ ደረስ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ዜጎቿ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ባሳሰበችበት የጉዞ ማስጠንቀቂያ ላይ በገንዘብ ችግር ከኢትዮጵያ መውጣት ለማይችሉ ዜጎቿ ብድር ሊመቻች እንደሚችል አስታውቃ ነበር።
"ዜጎችን ከአሜሪካ ለማውጣት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ ኢትዮጵያ የማብረር ዕቅድም የለም። በብዙ መልኩ የሚለየው በቅርቡ በአፍጋኒስታን ያካሄድነው አይነት ዜጎችን የማስወጣት እቅድ የለም" በማለት የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊው ተናግረዋል።
ስማቸው ያልተጠቀሰው ኃላፊ ይህንን ይበሉ እንጂ፤ በጂቡቲ የአሜሪካ ጦር አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ዊሊያም ዛና ከቀናት በፊት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤምባሲ ሠራተኞችን፣ አሜሪካውያንን እና የሌሎች አገራት ዜጎችን ከኢትዮጵያ ለማስወጣት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝርዝር የሆነ ዕቅድ በማውጣታቸት መዘጀታቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የውጭ አገራት መንግሥታት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ማሳሰብ የጀመሩት የህወሓት አማጺያን የደቡብ ወሎ ከተሞችን ተቆጣጠረው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳላቸው ካስታወቁ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ በኋላ ነው።
አንድ ዓመት የሞላው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋ ሲሆን በተለይ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በተለያዩ ቦታዎች ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው።
ይህንንም ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱና የክልል አስተዳደሮች የአማጺያኑን እንቅስቃሴ ለመመከት ለሕዝቡ ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።












