የአጎዋ የንግድ ዕድል መስተጓጎል በፋብሪካዎችና በሠራተኞች ላይ የፈጠረው ስጋት

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA
የአፍሪካ የእድገትና ዕድል ድንጋጌ በምኅጻረ ቃሉ አጎዋ ተብሎ በሚታወቀው የንግድ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ከሆኑ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ቆይታለች።
በዚህም በተለይ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ መላክ በመቻሏ በርካታ አምራች ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሥራ በመጀመራቸው ሺዎች የሚቆጠር የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባሻገር ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቶላታል።
የአጎዋ በስምምነት ተጠቃሚ አገራት በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ለመታቀፍ የሚያስችሉትን የተወሰኑ መመዘኛዎች እስካሟሉ ድረስ በግዛታቸው ያሉ አምራቾች ከታሪፍ ነጻ ምርታቸውን ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ ይፈቅዳል።
አሁን ግን በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አስከ መጪው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ድረስ መሻሻሎች ከሌሉ ኢትዮጵያ ስትጠቀምበት ከነበረው የአጎዋ ሥርዓት ውጪ እንደምትሆንና ሸቀጦችን ወደ አሜሪካ ከቀረጥ ነጻ መላክ መላክ እንድታቆም እንደሚደረግ ተገልጿል።
ይህ እርምጃ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት እንዲያበቃ ከምታደርጋቸው ግፊቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እርምጃው በጦርነት የተዳከመውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ ጫናን ሊያስከትል ይችላል።
በአጎዋ አማካይነት ወደ አሜሪካ የተለያዩ የአልባሳት ምርቶችን ከሚልኩ ፋብሪካዎች መካከል በደርዘን የሚቆጠሩት በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሠራተኞች ቀጥረው ያሰራሉ።
በአጎዋ በኩል በተመቻቸው ዕድል ቀደምት ተጠቃሚዎች ከሆኑት አንዱ የሆንግ ኮንግ ኤፒክ ግሩፕ አባል የሆነው ኤፒክ አፓሬልስ የተባለው የአልባሳት አምራች አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ በሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል እተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሳቢያ አሜሪካ፣ ኢትዮጵያን ከዚህ ከቀረጥ ነጻ እድል ተጠቃሚነት እንድትወጣ መወሰኗ ፋብሪካውን በእጅጉ አሳስቦታል።
"በኢትዮጵያ ሥራ የጀመርነው አገሪቱ ወይም ከሰሃራ በታች ያሉ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ምርታቸውን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ የማስገባት መብት በማግኘታቸው ነው። ስለዚህ ጉዳዩ በእርግጥም ያስጨንቀናል" ያሉት የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ራሂት ናይር ናቸው።
ይህ ውሳኔም ሥራቸውን በእጅጉ ስለሚጎዳው "አጎዋ ዕድል ከሌለ ወደ ሌላ አገር መሄድ ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራችን ከእንግዲህ አይጠቅመንም" ሲሉም አክለዋል።
ኤፒክ አፓሬልስን የመሳሰሉ ፋብሪካዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ቀጥረው ያሰራሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ አብዛኞቹ ሴቶች ሲሆኑ በአጎዋ ተጠቃሚነት ላይ የሚደረገው ገደብ መተዳደሪያቸውን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ለበርካታ ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ካስመዘገቡ አገር መካከል ቀዳሚዋ ናት።ኢትዮጵያ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በመገንባት የምጣኔ ሀብት ግስጋሴዋን ለማፋጠን በምትጥርበት ጊዜ ነው ጦርነት ያጋጠማትና ከአጎዋ ዕድል ለመታገድ የደረሰችው።
በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች የተስፋፋው ደም አፋሳሽ ጦርነት አንድ ዓመት ከማስቆጠሩ በላይ፤ ጦርነቱ የአገሪቱን ሀብት በማሟጠጠ ዕድገቷን አዝጋሚ አድርጎታል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማዕቀቦችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደሩን ቢቀጥልም ነግሩ የበለጠ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ጥሩወርቅ በኤፒክ አፓሬልስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ከሚሠሩ ሁለት ሺህ ያህል ሠራተኞች መካከል አንዷ ናት። የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ላለፉት አራት ዓመታት ቤተሰቧን የምታስተዳደረው በዚህ ድርጅት ተቀጥራ በምታገኘው ገቢ ነው።
"[ፋብሪካው] የሚዘጋ ከሆነ ወደ ቤት ተመልሼ ሥራ ፈት መሆን ይጠብቀኛል።…. አንዳንዴ ይህ ፋብሪካ ባይኖር እነዚህ ሁሉ ወጣቶች ምን ይሆናሉ ስል እራሴን እጠይቃለሁ" ስትል ጥሩወርቅ ፋብሪካው ለእሷና ለሌሎች ወጣቶች የፈጠረውን ዕድል ትገልጸዋለች።
"ሁሉም ወደ እናትና አባቶቻቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። ለእናቶቻቸው እና ለአባቶቻቸው እንደገና ሸክም ይሆናሉ" ትላለች።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትወጣ ያሳለፈችውን ውሳኔ "አሳዛኝ" ስትል የገለጸችው ሲሆን፤ እርምጃው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጉዳዩን በድጋሚ እንድታጤነው አሜሪካንን ጠይቃለች።
አጎዋ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን ለ100,000 ሰዎች በተለይም በጨርቃ ጨርቅ እና በአልባሳት ፋብሪካዎች ውስጥ ለሚሰሩ ሴቶች እና ወጣቶች በቀጥታ ሥራ ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ የቀጠለ ቢሆንም አሁንም ብዙዎች ሠላማዊ መፍትሔ እንደሚገኝና አገሪቱ ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት ተመልሳ ሥራቸውን እና መተዳደሪያቸውን ማዳን እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋሉ።
አጎዋ እንደ ከሃያ ዓመታት በፊት በአሜሪካ ኮንግረንስ የጸደቀ ሐሳብ ሲሆን ሲሆን ይህ የንግድ ዕድል ሥርዓት እንደ እአአ ከ2000 እስከ 2008 ድረስ እንዲተገበር ታስቦ የተጀመረ ነበር።
የታሰበለት የስምንት ዓመት ጊዜ ሲተናቀቅ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ አጎዋ እስከ 2015 እንዲራዘም ፈርመዋል። በማስከተልም እስከ 2025 እንዲራዘም ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የፈቀዱ ሲሆን ከአራት ዓመት በኋላ ክለሳ ይደረግበታል።















