በኢትዮጵያ ውይይት ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት የአውሮፓ ሕብረት እንደሚደግፍ አስታወቀ

የአውሮፓ ሕብረት

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ በኢትዮጵያ ውይይት ለማስጀመር የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ተገለጸ።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከሰሞኑ ባደረጉት ውይይት፤ በአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም በቀጠናው አገሮች አማካይነት በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት አማጽያን መካከል የውይይት በር ለመክፈት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተመልክቷል።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ "አንድ ዓመት ያለፈው ጦርነት የሰብዓዊ ቀውሱን አባብሶታል። ለጦርነቱ ወታደራዊ መፍትሔ የለውም" ብሏል።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስለ አውሮፓ እንዲሁም በመላው ዓለም ስላሉ ጉዳዮች ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው ስለ ሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትም የተነሳው።

የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ልዑክ ጆሴፕ ቦረል ፎንቴልስ "የአፍሪካ ሕብረት በኢትዮጵያ ውይይት እንዲጀመር እያደረገ ያለውን ጥረት እንደግፋለን" ብለዋል።

"ሁሉም ወገን ሰላም፣ መረጋጋት እና ደኅንነት በአገሪቱ እንዲሰፍን እንደሚፈልግ አስታውቋል። ከቃላት ባለፈ ጦርነቱን አቁሞ ለድርድር ዕድል መስጠት ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አድርጎ የወከላቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዘዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካዩ እስካሁን ስላከናወኗቸው ተግባራት እና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ነገሮች በአፍሪካ ሕብረት በኩል ባወጡት መግለጫ፤ ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር ካደረጉት ንግግር በተጨማሪ ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልል መሪዎች ጋር አበረታች ውይይት እንዳደረጉ ጠቅሰዋል።

ኦባሳንጆ "ጦርነት የፖለቲካዊ ውድቀት ነጸብራቅ ነው። ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ የለም። በጦር ሜዳ የሚገኝ ድል በኢትዮጵያ አስተማማኝ ፖለቲካዊ መረጋጋትን አያመጣም። ስለዚህም በውይይት ሰላም ለማምጣት ብቸኛው ዘላቂ እና አስተማማኝ መንገድ ነው" ማለታቸውም ይታወሳል።

የአፍሪካ ሕብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ አካላት ሁለቱም ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ ከኬንያው ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ውይይት ያደርጋሉ። በውይይታቸው ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንደሚያነሱም ይጠበቃል።

ኬንያታ ከቀናት በፊት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባዩ በኩል "ሰላም እንዲወርድ ህወሓት ከያዛቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች መውጣት አለበት። ለፌደራል መንግሥቱ ሕጋዊነት እውቅና መስጠት እና መቀበለ አለበት እንዲሁም ኃይሎቹ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ማቆም አለባቸው" ብሏል።

ህወሓት በበኩሉ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታን ጨምሮ ስልክ፣ መብራት፣ ትራንስፓርት እና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች በትግራይ እንዲመለሱ ሲል ቅድመ ሁኔታውን አስቀምጧል።

በጦርነቱ ምክንያት ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ በትክክል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሐዙ በሺዎች የሚቆጠር ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል።

ከዚህ ባሻገርም በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እርዳታን የሚሹ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ናቸው።

ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ገልጾ ነበር።