በአንድ ወቅት ኃያል የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዴት ተዳከመ?

የፎቶው ባለመብት, AFP
- ፀሐፊ, በፋሩክ ቾቲያ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ኒውስ
የኢትዮጵያ ጦር በአንድ ወቅት የአሜሪካን አክብሮትን ማግኘት የቻለ ጠንካራ ኃይል ነበር። ጦሩ በግንባር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ስለደረሰበት መንግሥት ተራ ዜጎች ከትግራይ አማፂያን ጋር ጦርነት በሚደረገው ጦርነት እንዲሳተፉ ጥሪ በማቅረብ ያልተለመደ እርምጃ ወስዷል።
ሠራዊቱ የነበረው አቅምም ላይ አስገራሚ ለውጥን ያሳየ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ ክልል ገዢ የነበረውን ህወሓትን ከሥልጣን ቢያስወግድም በአሁኑ ወቅት የቡድኑ ተዋጊዎች ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በሚወስዱ መንግዶች ላይ ያሉ ከተሞችን እየተቆጣጠሩ ነው።
"የህወሓት ታጣቂዎች በትግራይ ሽምቅ ውጊያ በመጀመሪያ ሠራዊቱን የጎዱት ጥቃት ፈጽሞ በመሸሽ ነው" በማለት መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ ፋይሰል ሮብሌ ያስረዳሉ።
"ከዚያም ለማጠናቀቅ ወደ ጦርነቱ ገቡ" ብለዋል።
ሆኖም የምጣኔ ሀብት ባለሙያውና የፖለቲካ ተንታኙ አቻምየለህ ታምሩ የህወሓት ግስጋሴ "ጊዜያዊ" ብቻ ነው ብለው ያምናሉ።
"ከየአቅጣጫው የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን አገሪቷን ለመከከላከል እና ለመታደግ እየተነሱ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የቢቢሲ ትግርኛ አርታኢ ሳሙኤል ገብረሕይወት የህወሓት ታጋዮች ስልት በኤርትራ ሽምቅ ውጊያ ወቅት የነበረውን ህይወት ያስታውሰዋል።
ከህወሓት ታጋዮች ጋር በመሆን የመንግሥቱ ኃይለማርያምን የደርግ ሥርዓት እስከተገረሰሰበት እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ተዋግተዋል።
"ቀለል ያሉ መሳሪያዎች የታጠቁ፣ በጣም ቀልጣፋ፣ በህይወት ማቆያ ምግብ የሚኖሩ እና ጥልቅ ጽናትና ቆራጥነት የሚያሳዩ" ነበሩ በማለት ቀደም ያሉ ታጋዮችን ያስታውሳል።
ኤርትራ ነፃነቷን አገኘች፣ ከአራት ዓመት በፊት የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የፖለቲካ የበላይነቱ ቢያበቃም ህወሓት በኢትዮጵያ ሥልጣንን ተቆጣጥሮ ቆይቷል።
አመራሮቹም ወደ ትግራይ የሄዱ ሲሆን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በተከሰተው ጦርነት በሠራዊቱ ውስጥ ባሉ ታማኝ አዛዦች እና ወታደሮች በመታገዝ በፌደራል መንግሥቱ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።
ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ክምችት መያዝ ብቻ ሳይሆን የተቃወሙ ከፍተኛ መኮንኖች እና ወታደሮች ተገድለዋል ወይም በሺዎች የሚቆጠሩትን ማርከዋል።
"በምሽት ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ኢትዮጵያ የፌደራል ጦር አልባ እንደትሆን የሚያደርግ ክፍተት ፈጥሯል" ይላሉ አቶ አቻምየለህ።
ሆኖም ጦሩ ከኤርትራ ሠራዊት በተገኘ ወሳኝ እርዳታ እና ከአማራ ክልል በተውጣጣው ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመታገዝ የአየር ድብደባ እና የምድር ላይ ውጊያ በመፈጸም ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ህወሓትን ከትግራይ ሥልጣን ማንሳት ችሏል።
ነገር ግን አቶ ሳሙኤል እንደሚለው ሠራዊቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መድፈር፣ ግድያና እህል ማቃጠልን ጨምሮ ሰፊ ግፍ ሲፈጽሙ "ከሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የትግራይ ተወላጆች ክብራቸውን ለማስጠበቅ ከህወሓት ጋር ተቀላቅለዋል።"
"ወላጆች ልጆቻቸው 'ቤት ውስጥ ከመሞት ይልቅ ሄዳችሁ ተዋጉ' ይሉ ጀመር። ጦርነቱ በትግራይ ሕዝብና በሠራዊቱ መካከል ሆነ፤ በህወሓትና በሠራዊቱ መካከል የተደረገ ጦርነት ብቻ አልነበረም" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደ ተንታኙ ገለጻ የቀድሞ ጄኔራሎች በጡረታ የተገለሉ ወይም የከዱ ወደ ትግራይ ተራሮችና ዋሻዎች በመሄድ የትግራይ መከላከያ ኃይልን በህወሓት ወታደራዊ ክንፍነት መሰረቱ። ይህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ምልምሎች በሚገባ የተደራጁ መሆናቸውንም ለማረጋገጥ ነው።
"እነዚህ ጄኔራሎች የትግራይ ተወላጆችን መጠበቅ ግዴታቸው እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ስለ ሠራዊቱ ባላቸው ዕውቀት አማካይነት የጦሩን ሽንፈቱ ወጠኑ" ይላሉ ተንታኙ።
የትግራይ ተዋጊዎች ከመዲናይቱ 300 ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ኃያል በነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ላይ የበላይነት እንዳላቸው ግልጽ ነው ሲሉም ያስረዳሉ።
"በአፍሪካ ቀንድ በሽብር ላይ በተነሳው ጦርነት በተለይም ከአልሻበብ በፊት በነበረው የሶማሊያ የእስልምና ፍርድ ቤቶች ሕብረትን ለመጣል ባደረገችው ሚና ኢትዮጵያ የአሜሪካ ቁጥር አንድ አጋር ነበረች። አሜሪካ ሠራዊቱን በገንዘብ ድጋፍ በመስጠትና በማስታጠቅ አልፎ ተርፎም ለወታደሮቹ ዝግጁ የሆኑ ምግቦችን ታቀርብ ነበር" ይላሉ።
ተንታኙ አክለውም "ጦሩ የአፍሪካ ሕብረት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ይተማመንበት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ራሷ ያልተረጋጋች እና ሠራዊቷም የቀድሞ ማንነቷ ጥላ ነው" በማለት ያስረዳሉ።
መክዳት እና ተስፋ መቁረጥ
በህወሓት ላይ ችግር የተከሰተው ከሁለቱ ትላላልቅ የኢትዮጵያ ብሔሮች ከኦሮሞ እና ከአማራ የተውጣጡ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረውን አመራር በመቃወም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለተቃውሞ መውጣቱን ተከትሎ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን መረከባቸውን ጋር ተያይዞ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባቀረቡት ጥልቅ ማሻሻያ ምክንያት ከህወሓት ጋር ቁርሾ ተፈጠረ።
"የትግራይ ተወላጆች ከአጠቃላይ ሕዝቡ 6 በመቶ ያህል ብቻ ሲሆኑ ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ብሔር ብሔረሰሶች የራሳቸው ክልላዊ መንግሥት የሰጣቸውንና በብሔር ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ ሥርዓት ፈጠረ" ይላሉ ተንታኙ።
አክለውም "ህወሓቶች ዐቢይ ስልጣንን በአሃዳዊነት መቆጣጠጠር እንደሚፈልጉ ተሰምቷቸው ነበር። በዚህም ምክንያት በመካከላቸው ከፍተኛ ፍጥጫ ተፈጠረ እና በመጨረሻም ወደ ጦርነት አመራ" ይላሉ።
መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የዓለም ሰላም ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር አሌክስ ደ ዋል በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደሮቻቸው ለእሳቸው ታማኝ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እና የትግራይ የበላይነትን በተመለከተ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በአዲስ መልክ መነሳታቸውን ይናገራሉ።
"የትግራይ ተወላጆች ከጠቅላላው ሠራዊት 18 በመቶ የነበሩ ሲሆን በከፍተኛ አዛዦች ደረጃ ሁለት እጥፍ ይሆናሉ።"
'ቁጥራቸው ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሲወዳደር ያልተመጣጠነ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይ ተወላጆችን በመግፋት ማሻሻያ ጀመሩ እና ለእሳቸው ታማኝ የሆኑ በኤምሬትስ የሰለጠኑ የሪፐብሊካን ዘቦችን ፈጠሩ" ሲሉ ፕሮፌሰር ደ ዋል ተናግረዋል።
"ለውጡ የሠራዊቱን ሞራል ጎድቶታል፣ እናም የተቀናጀ ኃይል መሆኑ ቀረ።ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልሶ ለማቋቋም ጊዜ አልነበራቸውም" ይላሉ ምሁሩ።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት በሠራዊቱ ውስጥ ካሉት 20 ክፍለ ጦሮች፣ ከነዚህ ውስጥ አስሮቹ እያንዳንዳቸው 5,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ያቀፉ የተሸነፉ ሲሆን ቢያንስ 10 ሺህ ወታደሮች መገደላቸውን እና ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው መማረካቸውን ያስረዳሉ። ቢቢሲ ከኢትዮጵያ መከላከያ ቃል አቀባይ አስተያየት ለማግኘት ቢሞክርም ምላሽ አልሰጡም።
የሰው ማዕበል ጥቃቶች
ህወሓት በሰኔ ወር አብዛኛውን የትግራይ ክፍል ከተቆጣጠረ በኋላ በአጎራባቾቹ አማራ እና አፋር ክልሎች ጦሩን በመላክ ጥቃት የከፈተ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም በምላሹ ሁሉም አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ አማፂያኑን ለማሸነፍ ሠራዊቱን እና ሚሊሻውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቀረቡ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የትግራይን ግስጋሴ ለማስቆም በአማራ ክልል ሠራዊቱ አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች እና የከተማ ወጣቶች በሰው ማዕበል ጥቃት አደራጅቷል። የተደራጀው ሕዝብ መሬታቸውን ለመከላከል ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸው፤ ነገር ግን መሠረታዊ ስልጠና የወሰዱት ለጥቂት ሳምንታት ብቻ ነው። እናም ከትግራይ መከላከያ ጋር እየተዋጉ ነበር " ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
"አንዳንድ ጊዜ፣ በሁለተኛው የሰው ማዕበል የመጡ ተዋጊዎች ጠመንጃ እንኳ አይኖራቸውም ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ምናልባትም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ - በትግራይ መከላከያ ኃይል ተገድለዋል" በማለት ያስረዳሉ።
"በተዋጊ እና በሲቪል መካከል ያለውን ልዩነት ስለሚያደበዝዝ የተወሳሰበ የሰብአዊ መብት ሁኔታን ይፈጥራል። በተጨማሪም በሕዝቦች መካከል ያለውን ጥላቻ ይጨምራል። በዚህ ጉዳይ ላይ በአማራ እና በትግራይ ተወላጆች መካከል ሰላምና እርቅን ለማምጣት አስቸጋሪ ያደርገዋል" በማለት አሌክስ ደ ዋል ይገልጻሉ።
አቻምየለህ ታምሩ ግን በፕሮፌሰሩ ሃሳብ አይስማማም ይህ ስልት ነው ሲሉ ይከራከራል፣ ለዚህም ወጣት ወንዶች ምንም አይነት ወታደር በማይኖርበት ጊዜ ከአማፂያኑ ጥቃት የሚደርስባቸውን ማኅበረሰቦች መከላከል ነበረባቸው።
"ህወሓት ቤት ለቤት እየዞረ አማሮችን ሲያድን፣ እናቶችን ሲጨፈጭፍና ሴት ልጆቻቸውን ሲደፍሩ ዝም ብለው እቤት መቀመጥ አልቻሉም" ይላል።
መንግሥት ጦርነቱን ለማሸነፍ ባደረገው የቅርብ ጊዜ እርምጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ "በወታደራዊ ዕድሜ ላይ ያለና ማንኛውም የጦር መሳሪያ ያለው ዜጋ" ወደ ጦርነት እንዲዘምት እና ጡረታ የወጡ መኮንኖችን ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠርቷል።
የአማራ ክልል መንግሥትም የራሱን መመሪያዎች በማውጣት ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዲዘጉ በማዘዝ ዜጎች የግል ተሽከርካሪዎቻቸውን ለግዳጅ እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
ፕሮፌሰር ደ ዋል እነዚህ እርምጃዎቹ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም ይላሉ ።
"ብዙዎችን ማሰባሰብ ይችላሉ ነገር ግን የሠራዊቱ ዕዝ እና የቁጥጥር መዋቅር ፈርሷል። ሠራዊት ማለት የጋራ ዓላማ፣ የጋራ አስተምህሮ እና የጋራ አሠራር ያለው ለዓመታት የተገነባ ተቋም ነው" ይላሉ።
ነገር ግን መቀመጫቸውን ካናዳ ያደረጉ የጸጥታ ባለሙያ የሆኑ ፕሮፌሰር ፊትዝ ጄራልድ የህወሓት ታጋዮች የከፋ ጉዳት እንደደረሰባቸው ያምናሉ። "የሰው ማዕበልን እንደ ተስፋ አስቆራጭ እርምጃ በመጠቀም ስትራቴጂካዊ መንገዶችን ለመቆጣጠር እና የመደራደር የበላይነትን ለመያዝ ሲጠቀምበት የነበረው ህወሓት ነው" ይላሉ።
ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት ቦታውን እንደያዘ ፕሮፌሰር ፊትዝ ጄራልድ ገልጸው የባሕር በር ለሌላት አገር ቁልፍ መዳረሻ የሆነችውንና ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚያመራው መንገድ ቅርብ የሆነችውን ሚሌ ከተማን ለመቆጣጠር ህወሓት ያደረጋቸው 12 ሙከራዎች መክሸፉን ከአገር ውስጥ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ይላሉ።
መያዝ ሳይሆን ድርድር
ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት አዲስ አበባን ከበባ ለማድረግ የታለመ ጥቃትም ላይ ህወሓት እየተሳተፈ ይገኛል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ህወሓት መንግሥት እንዲደራደር ጫና ማድረግ ይፈልጋል። አዲስ አበባ የሚገቡ አይመስለኝም። እዚያ በጣም ተወዳጅ አይደሉም" ይላል ሳሙኤል።
ፕሮፌሰር ደ ዋል "መንግሥት ወታደራዊ ሽንፈት ገጥሞታል። ነገር ግን ህወሓት ድል አደረግኩ ማለት አይችልም ምክንያቱም ማሸነፍ ፖለቲካዊ ነው" ይላሉ።
"በቂ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ተዋናዮች ድጋፍ እና ትብብር ያስፈልጋቸዋል ይህም የላቸውም" የሚሉት ፕሮፌሰር ደ ዋል እንደ አማራጭም፤ "ስለዚህ ድርድር መደረግ አለበት፣ የህወሓትም ትኩረት የትግራይን የወደፊት እጣ ፈንታ ማረጋገጥ ላይ ይሆናል።"












