በዓለም ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች ችላ ተብለዋል- ፖፕ ፍራንሲስ

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ በዓለማችን እየተፈጠሩ ላሉ ቀውሶችና ሰቆቃዎች ስሜት በማጣታችን፣ ትኩረት ሳያገኙ በርካታ አሳዛኝ ክስተቶች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ የገና በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ በአንዳንድ አፍሪካ አገራት፣ አውሮፓና እስያ እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶችን ጠቅሰዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ በጦርነት እየተናወጡ ላሉ እንደ ኢትዮጵያ፣ ዩክሬን፣ እንዲሁም ለአስር አመታት ያህል ከፅንፈኞች ጋር በሚደረገው ውጊያ ግጭት ላይ ያለውን የሳህልን ቀጠናን ጨምሮ ሰላም እንዲመጣ ጸሎት አድርገዋል።
"በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችን ለመፍታት ውይይቶች ችላ ተብለዋል። ለእነዚህ ውስብስብ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ አቋራጭ መንገዶችን ሲወሰዱ ይታያል።" ብለዋል ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ።
"በርካታ ጦርነቶች፣ ግጭቶች እና ቀውሶችንም እየተመለከትን ነው። በቅርቡ የሚቋጩም አይመስሉም። እኛም ችላ ብለናቸዋል።" ያሉት ፖፕ ፍራንሲስ አክለውም "እነዚህን አሳዛኝ ክስተቶች በጣም ስለለመድናቸው የዓለማችን ሰቆቃዎች በዝምታ እየታለፉ ነው" ብለዋል።
በተለይም በሶሪያ፣ ኢራቅና የመን ያሉ ጦርነቶችን ጠቅሰው "በርካቶች በዝምታ እያዩት ያሉት አሳዛኝ ሁኔታ ለዓመታት ያህል እየተፈጠረ ነው" በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ጠቁመዋል።
በእስራኤል እና በፍልስጥኤማውያን መካከል ለአስርት ዓመታት ያለው ቁርሾን አለም እንዲያስብ እንዲሁም በሊባኖስ ላይ ያለውን ታይቶ የማያውቅ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስም አለማቀፉ ማህበረሰብ አይዘንጋ ብለዋል።
በተጨማሪም ከአራት አስርት አመታት በላይ በጦርነት ክፉኛ እየተፈተኑ ያሉትን አፍጋኒስታንያውያንን በገና በዓል ያሰቧቸው ሲሆን አለምም የቻለውን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የአለምን ሰቆቃ ባሰቡበት በዚህ የገና በዓል ንግግራቸው በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት የተነሳባት የሚየንማርን ህዝብ በንግግራቸው ጠቅሰውታል። በሚየንማር እየተከሰቱ ባሉ አመፆችና፣ ሁከቶች የክርስትና እምነት ተከታዮችና የአምልኮ ቦታዎች ኢላማ እንዳይደረግ ጠይቀዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ጉዳት በአለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ ጥሎታል በማለት አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት በቤት ውስጥ ንግግራቸውን ያደረጉት ፖፕ ፍራንሲስ በዘንድሮው በአደባባይ ላይ ሆነው ንግግራቸውን አሰምተዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የካቶሊክ ምእመናን ማስካቸውን አጥልቀው በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የፖፑን ንግግር አድምጠዋል።
ቀደም ሲል የ85 ዓመቱ ፖፕ ፍራንሲስ የገና ዋዜማን በባዝሊካ ቤተክርስቲያን በቅዳሴ ያከበሩ ሲሆን ምዕመናኑ አቅም ለሌላቸው ድሆች የበለጠ ርሕራሄ እንዲያሳዩ እና "በሕይወት ውስጥ ለትንንሽ ነገሮች ዋጋ እንዲሰጡ" ምክር አስተላልፈዋል።
"በዚህ የፍቅር ምሽት አንድ ፍርሃት ብቻ ይኑረን ይህም የአምላክን ፍቅር መግፋት ነው። የእኛ ግዴለሽነትና ድሆችን መናቅ የእሱን ፍቅር መጉዳት ነው" ብለዋል።












