በማሊ የሩስያ 'ቅጥረኞች' መሰማራታቸውን ምዕራባውያን አወገዙ

የዋግነር ቅጥረኛ

ከ12 በላይ ምዕራባውያን አጋሮች ሩስያውን ቅጥረኛ ተዋጊዎች በማሊ ተሰማርተዋል ሲሉ አወገዙ።

በምዕራብ አፍሪካ ከጂሃዲስት ቡድኖች ጋር በሚደረገው ጦርነት ላይ በተጨማሪ የጸጥታውን ሁኔታ "ወደ ከፋ ደረጃ ሊያደርሰው ይችላል" ሲሉ ወቅሰዋል።

አስራ አምስት የአውሮፓ ሃገራት እና ካናዳ የዋግነር ቡድን አባል የሆኑ ቅጥረኛተዋጊዎች በማሊ ለማሰማራት ሩሲያ የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገች ነው ሲሉ ከሰዋል።

ሩሲያ በበኩሏ ዋግነር የተሰኘው የግል ወታደራዊ ኩባንያ ከማንኛውም የመንግሥት አካል ጋር ግንኙነት የለውም ስትል አስተባብላለች።

የዋግነር ቡድን በከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተሳትፏል በሚል የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ማዕቀብ ጥሎበታል።

ሚስጥራዊው የሩስያ ቅጥረኛ ተዋጊ ኩባንያ ማንነት ይፋ የሆነው በአውሮፓውያኑ 2014 ይህም ሩሲያን የሚደግፉ ተገንጣዮችን በምስራቃዊ ዩክሬን ግጭት በደገፉበት ወቅት ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በበርካታ እርስ በርስ ጦርነቶች ላይ ተሳታፊ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ከነዚህም መካል ሶሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሱዳን፣ ሊቢያና ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ይገኙበታል።

ሃገራቱ በያዝነው ሳምንት ሃሙስ እለት ባወጡት መግለጫ የዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎች በማሊ መሰማራታቸው "የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ሊያባብሰው ይችላል እንዲሁም በግጭት እየተበጣበጠች ባለችው ሃገር ውስጥ የሰላምና የእርቅ ስምምነቱን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የማሊ ባለስልጣናት የሃገሪቱን የታጠቁ ሃይሎች ከመደገፍ ይልቅ ለውጭ ቅጥረኛ ወታደሮች ለመክፈል ቀድሞውንም ቢሆን የተመናመነ የህዝብ ገንዘብ መጠቀማቸው በጣም የሚያሳዝን ነው ብለዋል።

መግለጫውን ያወጡት አገራት ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ሊትዌኒያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ፖርቱጋል፣ ሮማኒያ እና ስዊድን እና ዩናይትድ ኪንግደም ናቸው።

የቀድሞዋ የማሊ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ በቅርቡ በሰሜናዊ ማሊ ከሚገኘው የጦር ሰፈር ለመጨረሻ ጊዜ ለቃ ወጥታለች።ፈረንሳይ በሳህል ክልል እስላማዊ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ያሰፈረቻቸው ሰራዊት ናቸው።

ማሊ እስካሁን አዳዲስ በተከሰቱ ጉዳዮች ላይ ምንም ይፋዊ አስተያየት አልሰጠችም።

1px transparent line