የሱዳን ሴቶች በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀም ጾታዊ ጥቃትን በመቃወም አደባባይ ወጡ

ተቃውሞ የምታሰማ ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሱዳን እሁድ ዕለት በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ 13 ሴቶችና ልጃገረዶች መደፈራቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ጾታዊ ጥቃትን በመቃወም አደባባይ ወጡ።

የተባበሩት መንግሥታትም የአገሪቱ የፀጥታ ኃይል አባላት ወታደራዊ አስተዳዳሩን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸሙ የሚያመለክቱ 'የሚረብሹ ሪፖርቶች' ደርሰውኛል ብሏል።

አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ሴቶች ተቃውሞ እንዳያሰሙ ለማድረግ ወሲባዊ ጥቃትን መጠቀምን ተችተዋል።

የፀጥታ ኃይሎች በቀረበባቸው ክስ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ጥቅምት ወር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ ዴሞክራሲን በመደገፍ በሱዳን በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ሴቶች ግንባር ቀደም ሆነዋል።

በዋና ከተማዋ ካርቱምና በኦምዱርማን ሐሙስ ዕለት በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ ላይም "መደፈር አያስቆመንም!" እና "የሱዳን ሴቶች አይበገሩም!" የሚሉት መፈክሮች ማሰማታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ባወጡት የጋራ መግለጫ የሴቶችን ድምጽ ለማፈን ወሲባዊ ጥቃትን እንደ መሣሪያ መጠቀምን አውግዘዋል።

መግለጫው በዩናይትድ ኪንግደም፣ በኖርዌይ፣ ሰዊትዘርላንድ እና ካናዳ የተፈረመ ሲሆን ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

እሁድ ዕለት በተካሄደውና መፈንቅለ መንግሥቱን ለማውገዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሳተፉበት ሰልፍ ላይ ሁለት ሰዎች መገደላቸውም ተነግሯል።

የዲሞክራሲ ደጋፊዎች እአአ በ2019 ለረዥም ጊዜ አገሪቷን ሲመሩ የነበሩትን ኦማር አልበሽር ከሥልጣን እንዲወገዱ ምክንያት የሆነውን አብዮት ወታደሮቹ በመጥለፋቸው ይከሳሉ።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሐን ጥቅምት ወር ላይ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የፖለቲካ ቡድኖች ሲቪሎችን በፀጥታ ኃይሉ ላይ ሲያነሳሱ ነበር በማለት "በአገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል የተወሰደ እርምጃ ነው" ሲሉ ራሳቸውን ተከላክለዋል።

ጄነራሉ እአአ 2023 ሊካሄድ በታቀደው ምርጫ ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸጋገር አሁንም ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደባቸው በኋላ ባለፈው ወር ወደ ሥልጣናቸው ከተመለሱት የሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በደረሱት ስምምነት መሠረትም ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የባለሙያዎችን ካቢኔ አዋቅረው ይመራሉ።

ይሁን እንጂ አዲሱ የሲቪል መንግሥት በወታደራዊ ኃይሉ ክትትል ሥር በመሆኑ ምን ያህል ሥልጣን ይኖረዋል የሚለው ግልጽ አይደለም።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ በርካታ መላምት እየተሰጠ ነው።

አንዳንድ ሪፖርቶች ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ማቀዳቸውን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ሥልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ ጄኔራል አልቡርሐን እንዳሳመኗቸው ይናገራሉ።