ላይቤሪያ ውስጥ ጨቅላ ልጇን ሸጣለች የተባለች እናት በፖሊስ ተያዘች

A woman in handcuffs

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንዲት የ26 ዓመት ላይቤሪያዊት እናት ልጇን ሸጣለች በሚል በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ተጠርጥራ በፖሊስ መያዟ ተዘገበ።

ላይቤሪያዊቷ እናት የአምስት ወር ጨቅላ ልጇን ለአንዲት ለማታውቃት ሴት ሸጣለች የተባለችው በ60 ዶላር ሲሆን በዚህም ድርጊቷ ክስ ተመስርቶባታል።

ልጇን ለማሳደግ ችግር ላይ እንደነበረች የተገለጸው እናት ምናልባት ያለችበት ሁኔታ ይህንን እንድታደርግ ሳያስገድዳት እንዳልቀረ ተገምቷል።

ነገር ግን እናት ልጇን ሸጠች መባሉንና በፖሊስ የቀረበባትን ክስ የተቃወመች ሲሆን ልጇን በገንዘብ እንዳልቀየረች ገልጻለች።

የፖሊስ የክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው ተከሳሿ የተያዘችው የህጻኑ ልጅ አባት ባቀረበባት ክስ አማካይነት ነው።

እናት ባለባት ችግር ምክንያት ህጻኗን ለሌላ ግለሰብ አሳልፋ መስጠቷን እንጂ እንደተባለው ገንዘብ ተቀብላ እንዳልሸጠች ለመርማሪዎች ተናግራለች።

ነገር ግን ህጻኗን ላልታወቀች ግለሰብ እንዲሰጥ አመቻችቷል የተባለ ግለሰብ፤ እናት ገንዘብ መቀበሏን ለፖሊስ መስክሯል።

የጨቅላ ልጇን ፍላጎት በማሟላት ለማሳደግ ችግር ላይ እንደነበረች የተናገረችው እናት፤ ልጇን ለማታውቃት ሰው ለመስጠት መስማማቷን ገልጻለች።

እናት እንደምትለው ጠቁሞ ያስያዛት የህጻኗ አባት ልጁን ለማሳደግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባለመወጣቱ ብቻዋን ጥረት ብታደርግም ህይወት በጣም ከባድ እንደሆነባት ተናግራለች።

"ልጄን አልሸጥኩም። በችግር እየኖርኩ ስለሆነ ተንከባክባ እንደምታሳድግልኝ ቃል ለገባችልኝ ሴት ነው የሰጠኋት" ብላለች።

ፖሊስ ባደረገው ምርመራ እናትየውን በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር እንዲሁም ልጇን እንድትሸጥ ረድቷታል የተባለው ግለሰብ ደግሞ በተባባሪነት በአገሪቱ ሕግ መሠረት ክስ መስርቶባቸዋል።