የናይጄሪያ መንግሥት ሙስናን ለመከላከል ለፖሊሶች የደሞዝ ጭማሪ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የናይጄሪያ መንግሥት በአገሪቱ የፖሊስ መኮንኖች ዘንድ የተስፋፋውን ሙስና ለመከላከል ሲል የ20 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ አፀደቀ።
ፕሬዚደንት ሙሐመዱ ቡሃሪ ባለፈው ዓመት የፖሊስን የጭካኔ ድርጊት በመቃወም የተካሄዱ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ተከትሎ የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር።
የአገሪቱ የፖሊስ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሐመድ ማጋሪ ዲንግያዲ ረቡዕ ዕለት ከካቢኔ ስብሰባ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የደመወዝ ጭማሪው የፖሊስ መኮንኖች ጉቦ እንዳይቀበሉና ዜጎችን እንዳይመዘብሩ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ አካል ነው።
ሚኒስትሩ አክለውም ውሳኔው በፖሊስ እና በሕዝቡ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ያለመም ነው ብለዋል።
የደመወዝ ጭማሪው ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ለጀማሪ የፖሊስ አባላትም ከደሞዝ ላይ የሚቆረጥ ግብር እንዲነሳ የተደረገ ሲሆን ይህም ወደ ኋላ ተመልሶ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ጸድቋል።
የአገሪቱ ልዩ የፖሊስ ኃይልን በመቃወም ሲካሄድ የነበረው እንቅስቃሴ የተቀሰቀሰው ፖሊስ በተለይም የፀረ ዘረፋ ልዩ የፖሊስ ኃይል (ሳርስ) ማሰቃየትን፣ ግድያና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ይፈፅማሉ የሚል ክስ በመበራከቱ ነበር።
ይህን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎም ልዩ የፖሊስ ቡድኑ እንዲበተን የተደረገ ሲሆን፣ በተለያዩ በርካታ ግዛቶች ከተቃውሞ ሰልፎቹ ቀድሞም ሆነ በተቃውሞው ወቅት በፀጥታ ኃይሎቹ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመረምር አጣሪ ቡድን ተቋቁሟል።
ይሁን እንጂ ተሟጋቾች ከአንድ ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ በጥቃቱ እጃቸው ያለበት የፖሊስ አባላት እስካሁን ተጠያቂ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።












