ኒው ዚላንድ ከ2008 ወዲህ ለተወለዱ ዜጎቿ ሲጋራ እንዳይሸጥ አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኒው ዚላንድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2008 ወዲህ ለተወለዱ ዜጎቿ ሲጋራ መሸጥን የሚያግድ ሕግ አውጥታለች።
ከ2008 ወዲህ የተወለደ ማንኛውም ኒው ዚላንዳዊ የሲጋራ ምርቶችን በአጠቃላይ እስከ ዕድሜ ዘመኑ መጨረሻ ድረስ መግዛት አይችልም።
በዚህም አገሪቱ በጊዜ ሂደት በግዛቷ ውስጥ ሲጋራ ማጨስን ለመከልከል አቅዳ የተለያዩ እርምጃዎችን እወሰደች ነው።
የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አይሻ ቨርል "ወጣቶች ማጨስ እንዲጀምሩ አንፈልግም" ብለዋል።
የኒው ዚላንድ ሐኪሞች እና የጤና ባለሙያዎች አዲሱን ሕግ "ከዓለም ግንባር ቀደም" ሲሉ አሞግሰዋል።
ሕጉ የሲጋራ አጫሶችን ቁጥር ከመቀነሱም ባሻገር ሲጋራ ውስጥ የሚገባውን የኒኮቲን መጠን በመገደብ ረገድም ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በኦታጎ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ጃኔት ሁክ እንደሚሉት፤ ሕጉ ሰዎች ሲጋራ ማጨስ እንዲያቆሙ ወይም ደግሞ ጤናቸውን ወደማይጎዱ ምርቶች ፊታቸውን እንዲያዞሩ ይረዳል።
በተለይም ቀጣዩ አገር ተረካቢ ወጣት ትውልድ በሲጋራ ሱስ እንዳይጠመድ ለማድረግ የወጣ ሕግ ነው።
አንድ ነዋሪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል "ጥሩ እርምጃ ነው። ዛሬ ዛሬ ታዳጊዎች ሲያጨሱ መመልከት እየተለመደ መጥቷል። እኔም ገንዘብ እንዳላባክን የሚረዳኝ ሕግ ነው" ብለዋል።
በሌላ በኩል ሲጋራን በመደበኛ ገበያ ማገድ ለትይዩ ጥቁር ገበያ መነሻ ይሆናል ብለው የሚሰጉም አልታጡም።
ይህንን ስጋት አስቀድሞ የተረዳው የጤና ሚንስቴር፤ ሲጋራ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ ቁጥጥር እንደሚደረግ አስታውቋል።
የመደብሮች ማኅበር ሊቀ መንበር የሆኑት ሰኒ ኩሻል፤ ሕጉ "መቶ በመቶ ንድፈ ሐሳብ እና ከተግባራዊነት የራቀ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
ሲጋራ በመደብር መሸጥ ሲቆም የሚፈጠረውን ክፍተት ወንጀለኞች እንደሚጠቀሙበት ይገምታሉ።
ኒው ዚላንድ እስከ 2025 ድረስ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር ወደ 5 በመቶ የመቀነስ ዕቅድ ነድፋለች። በጊዜ ሂደት ደግሞ ሲጋራን ሙሉ በሙሉ የማስወገድ አላማ አላት።
አገሪቱ በአሁኑ ወቅት 13 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿ አጫሽ ናቸው። ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነው በቀደምት ነዋሪዎቹ የሞሪ ማኅበረሰቦች ዘንድ ነው።
የሞሪ ማኅበረሰብ አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ለሕመም እና ሞት ይጋለጣሉ።
ሲጋራ በኒው ዚላንድ ከአራት የካንሰር ሕመሞች ለአንዱ ምክንያት እንደሆነ የጤና ሚንስቴር ገልጿል።
ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ከተጋለጠው 5 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል አብዛኛው አጫሽ ነው።
የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች የሲጋራ ምርትን ለማዳከም የተለያዩ ደንቦችን አውጥተዋል።
አዲስ የወጣው ሕግ ሲጋራ የት እንደሚሸጥ የሚወስን ሲሆን፤ በመደብር እና በሱቅ በደረቴ ሲጋራ እንዳይሸጥ ይከለክላል።
አሁን ላይ ሲጋራ መሸጥ የተፈቀደላቸው መደብሮች 8,000 ሲሆኑ፤ በአዲሱ ሕግ መሠረት ቁጥሩ ወደ 500 ዝቅ እንዲል ይደረጋል።
በወጣቶች ዘንድ ከመደበኛው ሲጋራ ይልቅ ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ማጨስ (ቬፒንግ) እየተዘወተረ መጥቷል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ ለካንሰር የሚያጋልጥ ፈሳሽ አለው።
ኒው ዚላንድ 2017 ላይ ባወጣችው ሕግ፤ መደበኛ ሲጋራን ለመቀነስ ወደ ቬፒንግ መዞርን እንደ አማራጭ አቅርባ ነበር።












