ሲጃራ የሚያጤሱም ሆኑ ያቋረጡ 'የሚኖሩት በከፍተኛ በስቃይ ነው'

የተለኮሰ ሲጋራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሲጃራ የሚያጤሱም ሆነ ማጤስ ያቆሙ የሲጃራ ሱስ ከሌለባቸው ሰዎች አንጻር ሲታዩ የሚኖሩት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆኑን አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።

ጥናቱ የተደረገው 220 ሺህ ሰዎች ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ለስቃዩ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ምን እነደሆነ አላወቅንም በማለት ነገር ግን ሲጋራ ማጨስ ሰውነታችን ላይ ቋሚ ለውጥ ያስከትላል ሲሉ ተናግረዋል።

የፀረ ሲጃራ ቡድኖች ደግሞ ይህ ምኑ ይደንቃል ሲሉ ግኝቱ እንደ ትልቅ ነገር መታየት እንደሌለበት ተናግረዋል።

ተመራማሪዎች ከ2009 እስከ 2013 ድረስ የተሰበሰበ መረጃን መሰረት አድርገው ጥናታቸውን አከናውነዋል።

አጢሰው የማያውቁ፣ በቀን አንዴ ያጤሱ ከነበሩ ወይንም ደግሞ አሁን እያጤሱ ያሉ በሚል ከፍለው ማጥናታቸውን ያስረዳሉ።

ጥናቱ የተደረገባቸው ግለሰቦች ምን ያህል ሕመምና ስቃይ እንደሚሰማቸው የተጠየቁ ሲሆን፣ የሚሰማቸው ሕመምንም ከ 0 እስከ 100 ድረስ ደረጃ ሰጥተውታል።

የሚሰጡት ቁጥር ከፍ ባለ ቁጥር ስቃዩም ከፍ ያለ ይሆናል ማለት ነው።

አሁን የሚያጤሱ አልያም ያጤሱ የነበሩ ግለሰቦች አጢሰው ከማያውቁ ሰዎች አንጻር ሲታዩ፣ የሰጡት ነጥብ በአንድ ወይንም በሁለት ነጥብ ከፍ ያለ መሆኑን የጥናት ቡድኑ ይፋ አድርጓል።

"የግኝታችን ዋና ፍሬ ነገር ማጤስ ያቆሙ ሰዎች አሁንም ድረስ ህመሙ እንደሚሰማቸው ማወቃችን ነው" ብላለች ዶ/ር ኦልጋ ፐርስኪ ለቢቢሲ።

ዶ/ር ፐርስኪ አክላም ከግኝታቸው ሁሉ ይበልጥ ያስደነቃት ከፍተኛ ሕመም የሚሰማቸው ሆነው የተገኙት እድሜያቸው ከ16-34 ድረስ ያሉ ወጣት አጢያሾች መሆናቸው ነው።

ማጤስ ባቆሙ ሰዎች ላይ እስካሁን ድረስ ህምመ ሊሰማቸው የቻለበትን ምክንያት ፍርጥርጥ አድርጎ ማብራራት የተሳነው ይህ ጥናት መላምት ነው ያለውን ግን አስቀምጧል።

አንደኛው መላምት በትምባሆ ውስጥ ያለው ኬሚካል በቋሚነት የቲሹ ጉዳት ስለሚያስከትል ሊሆን ይችላል የተባለ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ሲጋራ ማጤስ በሰውነታችን የሆርሞን ስርዓት ላይ ቋሚ ጉዳት ሊያስከትል መቻሉ ነው።

ሲጃራ ማጤስ የሳንባ ካንሰርን እንደሚያመጣ የተረጋገጠው እኤአ በ1950ዎቹ ሲሆን ከዚያ በኋላ በተደረጉ ምርምሮች አጢያሾች የሚደረግላቸው ሕክምና ውጤታማ እንዳይሆን እንደሚያደርግም ተረጋግጧል።

አጢያሾች በካንሰር፣ በልብ፣ በመተንፈሻ አካል፣ የመስማትም ሆነ የስኳር ሕምም ቢገጥማቸው ታክመው ለመዳን ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል።

አጫሾች የቀዶ ጥገና ህክምና ከተደረገላቸውም በኋላ ለማገገም ከፍተኛ ጊዜ ይፈጅባቸዋል።