ሩስያ በረንዳ ላይ ማጤስ ከለከለች

በአገሪቱ አዲስ እየተረቀቀ ባለው የእሳት አደጋ መከላከያ መመሪያ መሰረት፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች በረንዳ ላይ ሲጋራ ማጤስ አይቻልም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአገሪቱ አዲስ እየተረቀቀ ባለው የእሳት አደጋ መከላከያ መመሪያ መሰረት፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች በረንዳ ላይ ሲጋራ ማጤስ አይቻልም

ሩስያ በረንዳ ላይ ማጤስ መከልከሏ ተሰምቷል። በአገሪቱ አዲስ በተረቀቀው የእሳት አደጋ መከላከያ መመሪያ መሰረት፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች በረንዳ ላይ ሲጋራ ማጤስ አይቻልም።

አዲሱ መመሪያ፤ ሰዎች በሚሰባሰቡበት የትምህርት ቤት መኝታ ክፍል እና በሆቴል የእንግዳ መቀበያ ውስጥ ሲጋራ ማጤስ ይከለክላል። በረንዳ ላይ ክባብ የተባለውን ምግብ ማዘጋጀት እና ሻማ ማብራት እንደማይቻልም ተዘግቧል።

ሲጋራ ማጤስ እንዲሁም ክብሪት መለኮስም ለእሳት አደጋ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሩስያ ባለሥልጣኖች የተናገሩ ሲሆን፤ መመሪያውን ጥሶ የተገኘ ግለሰብ፤ 47 ዶላር (3,000 ሩብል) ይቀጣል ተብሏል።

በርካታ ሩስያውያን ሲጋራ የሚያጠሱት በረንዳ ላይ ሲሆን፤ መመሪያው ተግባራዊ ሲደረግ በጋራ መኖሪያ ህንጻዎች የምድር ቤት ለማጤስ ይገደዳሉ።

አዲሱ መመሪያ ያልተዋጠላቸው ሩስያውያን "መንግሥት ሰዎች በገዛ ንብረታቸው እንዳይጠቀሙ እያደረገ ነው፤ በረንዳ ላይ ካልተጤሰ ታዲያ የት ይኬዳል?" ሲሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አስተያየታቸውን ጽፈዋል።

የሩስያ የሲጋራ አጫሾች መብት ተሟጋች ኃላፊ አንድሬይ ሎስክቶቭ፤ "መንግሥት ሲጋራ ማጤስ መከልከል የሚችልበት ቦታ ሁሉ እንዳይጤስ ከልክሏል። የቀረው በረንዳ ላይ ማጤስ ነበር፤ አሁን ግን እሱም ተከለከለ" ብሏል።