የቤት ውስጥ አየር መበከል ለጤናችን ጠንቅ እንደሚሆን? አምስት የመፍትሄ ሃሳቦችን እነሆ

በቤት ውስጥ የሚያጨሱ ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቤት ውስጥ ሲጋራ ማጨስ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው

የአየር ብክለት ለብዙ ሃገራት ፈተና እየሆነ የመጣ ጉዳይ ሲሆን፤ በየዓመቱ እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከዚህ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያልፋል።

አሁን እየኖርንበት ባለው ዓለም ከአስር ሰዎች ዘጠኙ ሲተነፍሱ የሳንባ ካንሰርን ለመሳሰሉ በሽታዎች ይጋለጣሉ።

እነዚህ በአይን የማይታዩ በካይ ንጥረ-ነገሮች በቤት ውስጥ ስንሆን ደግሞ ጉዳታቸው ከፍተኛ ነው። አዲስ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረትም በቤት ውስጥ የሚከሰት ብክለት የሚያደርሰው ጉዳት ከውጪው ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እስከ አምስት እጥፍ ይበልጣል።

ነገር ግን ይህንን ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም አሉ። እንዚህ አምስት የመፍትሄ እርምጃዎች በቤት ውስጥ ሊያጋጥመን የሚችልን ብክለት ለመከላከል ጠቃሚ ምክሮኦች ናቸው።

1. አየር እንደልብ ዘዋወር ያድርጉ

አየር በቤት ውስጥ በደንብ የማይንሸራሸር ከሆነ፤ በካይ ንጥረ-ነገሮች በቤት ውስጥ ይቀራሉ።

የቤት ውስጥ በሮችና መስኮቶች ቢያንስ በቀን ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ቢከፈቱና ለሃያ ደቂቃዎች ቤቱ ቢናፈስ፤ በካይ የሆኑት ንጥረ-ነገሮች ከአዲሱ አየር ጋር ተቀላቅለው የመውጣት እድላቸው ሰፊ ይሆናል።

ከዚህ በተጨማሪም ምግብ ካበሰሉ በኋላና ገላዎትን ከታጠቡ በኋላም ቤትዎን ማናፈስ ተገቢ ነው።

በመስኮት በኩል አየር የምትቀበል ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቤትን በርና መስኮት በመክፈት አየር እንዲዘዋወር ማድረግ

2. ቤት ውስጥ ተክሎች እንዲኖሮ ያድርጉ

ቤትን በአትክልት መሙላት ከሚኖረው ጥቅም በተጨማሪ ለመመልከትም ማራኪ ነው።

አንዳንድ ተክሎች በአየር ውስጥ የሚገኙ ጎጂ ንጥረ-ነገሮችን የማስወገድ አቅም ያላቸው ሲሆን፤ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን አፍኖ በመያዝ ለአካባቢያችንም ከፍተኛ ጠቀሜታን ያበረከታሉ።

ነገር ግን በቤታችን ውስጥ የምናስቀምጣቸው ተክሎች እንክብካቤ የማናደርግላቸው ከሆነ፤ እንደውም ጎጂ የሆኑ ንጥረ-ነገሮችን ወደ አየር ሊለቁ ይችላሉ።

ስለዚህ ሁሌም ቢሆን ሌላው ቢቀር ውሃና ጥሩ አየር እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል።

3. ሽታ ያላቸው ፈሳሾችን ያስወግዱ

በማንኛውም ጊዜ በቤት ውስጥ የሚጠቀሟቸው ሽቶዎች፣ ዲኦድራንቶችና የአየር ጠረን መቀየሪያ ምርቶች ትተውት የሚሄዱት ጎጂ ንጥረ-ነገር አለ።

ይህ ደግሞ ሰውነታችን ላይ በተለይ ደግሞ ሳንባችን ላይ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው።

የተለያዩ አይነት የቤት ውስጥ ተክሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተለያዩ አይነት የቤት ውስጥ ተክሎች መትከል

4. በቤት ውስጥ ሲጋራ አያጭሱ

ማጨስ በራሱ ከፍተኛ ጉዳት ያለው ሲሆን፤ ቤት ውስጥ ማጨስ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደማለት ነው።

የሲጋራ ጭስ በቤት ውስጥ ሲጠራቀም በተለይ ደግሞ በሮች ተዘግተው ከሆነ የሚኖረው ጉዳት እንኳን ለማያጨስ ሰው፤ ለሚያጨሰው ሰው በራሱ ከፍተኛ ጉዳት አለው።

በቤት ውስጥ ሲጋራ ከሚያጨሱ ቤተሰቦች የሚወለዱ ህጻናት ደግሞ ለድንገተኛ ሞት የተጋለጡ ናቸው።

5. የቤትዎን ንጽህና ይጠብቁ

  • አልጋዎትን በየቀኑ ያጽዱ
  • በቤትዎ ውስጥ እርጥበት ይቀንሱ
  • ምንጣፍዎን ቶሎ ቶሎ ያጽዱ
  • የልብስ ማጠቢያ ማሸን የሚጠቀሙ ከሆነ ከመስኮት አጠገብ ያድርጉት
  • በበርዎ ስር ቆሻሻ እንዳይገባ መከላከያ ያዘጋጁ