2019፡ የአውሮፕላን አደጋ ተጎጂዎች ቁጥር የቀነሰበት ዓመት ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንጆቹ 2019 በአውሮፕላን አደጋ የሚጎዱ ሰዎች ቁጥር በ50 በመቶ የቀነሰበት ዓመት ነው ተባለ።
ቱ70 የተባለ የበረራ ኢንዱስትሪ ጥናት አካሂያጅ ድርጅት፤ ባለፈው ዓመት በአውሮፕላን አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር 257 ሲሆን ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት [2018] ግን 534 እንደነበር ዘግቧል።
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከባድ የሚባል አደጋ ቢደርስበት በጠቅላላው በዓመቱ የተመዘገበው አደጋ ብዛት በተነፃፃሪ ዝቅ ያለ ነው።
እንደ ጥናቱ ከሆነ በአውሮፕላን አደጋ የሚመዘገቡ አደጋዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት መቀነስ እያሳየ ሲሆን የአውሮፕላን በረራዎች ደግሞ እጅግ እየጨመሩ መጥተዋል።
ድርጀቱ ባደረገው ጥናት መሠረት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 86 አደጋዎች ትላልቅ በሚባሉ የንግድ አውሮፕላኖች ላይ የደረሰ ሲሆን፤ 8 ከባድ አደጋዎች ተከስተው 257 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።
ከጠቅላላው የዓመቱ 257 ተጎጂዎች መካከል 157 ሰዎች ያለቁት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ መከስከስ ምክንያት ነው።
በዓለማችን ከሚከወኑ 5.58 ሚሊዮን የትላልቅ ንግድ አውሮፕላን በረራዎች መካከል አንድ ከበድ ያለ አደጋ ደርሷል።
አቪዬሽን ሴፍቲ ኔትዎርክ የተሰኘ ተቋም ያለፈው ዓመት በንግድ አውሮፕላን በረራ ኢንዱስትሪው የተሻለ የሚባለው ነው ሲል ተደምጧል። ቢሆንም 2017 በበረራ ታሪክ 13 ጉዳቶች ብቻ የተመዘገቡበት ሆኖ አልፏል።
ጥናቱ ትላልቅ የንግድ አውሮፕላኖችን ብቻ አካቶ የተሠራ ሲሆን አነስተኛ አውሮፕላኖች አልተካተቱበትም። አልፎም ወታደራዊ፣ የልምምድ እና የግል አውሮፕላኖች በጥናቱ ውስጥ አልተካተቱም።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኔዥያው ላየን አየር መንገድ ላይ የደረሱት ሁለት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋዎች በበረራ ኢንዱስትሪው ላይ በጎ የማይባል አሻራ ጥለው አልፈዋል።













