ቦይንግ " ከእንግዲህ የሚታመን ድርጅት አይደለም" በአደጋው አባቷን ያጣችው ዚፖራ ኩርያ

የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ሲከሰከስ አባቷን ያጣችው ዚፖራ ኩርያ "ቦይንግ ከዚህ በኋላ የሚታመን ድርጅት አይደለም" ብላለች።
ዚፖራ ከአውሮፓ የበረራ ተቆጣጣሪ ጋር ትላንት ስትገናኝ "ቦይንግን እምነት የሚል ቃል ባለበት አልጠራውም" ስትል ተናግራለች።
ቦይንግ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሁለት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ከተከሰከሱ በኋላ፤ 737 ማክስን አግዷል። የድርጅቱን ስም ለማደስም እየተጣጣረ ይገኛል።
የቦይንግ ቃል አቀባይ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በላየን ኤር ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች፤ ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን አንደሚመኙ ገልጸው፤ "ለተሳፋሪዎቻችን እና ለሠራተኞቻችን ደህንነት ቅድሚያ እንሰጣለን" ብለዋል።
ዚፖራ ኩርያ፤ ቦይንግ 737 ማክስ ተገቢው ፍተሻ ሳይደረግበት ዳግመኛ እንዳይበር ለመጠየቅ ሌሎች ቤተሰቦቻቸውን በአደጋው ካጡ ግለሰቦች ጋር በመሆን የአውሮፓ የበረራ ተቆጣጣሪን (ዩሮፕያን ሴፍቲ ኤጀንሲ) አግኝታለች።
በቦይንግ ማክስ 737 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የዚፖራን አባት ጨምሮ 156 ሰዎች ሞተዋል። በላየን ኤር አደጋ ደግሞ 189 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የአውሮፓ የበረራ ተቆጣጣሪ ዋና ዳይሬክተር ፓትሪክ ካይ፤ ቦይንግ 737 ማክስ ለአውሮፓ በረራ ብቁ ከመባሉ በፊት ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርጉ እንደገለጹላት ዚፖራ ተናግራለች።
ዋና ዳይሬክተሩ፤ የአሜሪካ በረራ ተቆጣጣሪ (ኤፍኤኤ) እንዲሁም ቦይንግ ጫና ለማሳደር ቢሞክሩ እንኳን ከአቋማቸው ፈቀቅ እንደማይሉ እንደነገሯትም አክላለች።
ቦይንግ፤ የአሜሪካ በረራ ተቆጣጣሪው 'ፌደራል አቪየሽን አድምንስትሬሽን' (ኤፍኤኤ)፤ ማክስ አውሮፕላኖች በሚቀጥለው ዓመት ዳግመኛ እንዲበሩ እንደሚፈቅድ ተስፋ አድርጓል።
"ሊነገሩን የሚገቡ ነገር ግን የተደበቁ ብዙ ነገሮች አሉ። ታይተው እንዳልታዩ መታለፍ ያልነበረባቸው ነገሮችም አሉ። በየጊዜው ችሎት ስንሄድና ከበረራ ኃላፊዎች ጋር ስንነጋገር አደጋውን መግታት ይቻል እንደነበር ተገንዝበናል፤ የምንወዳቸውን ሰዎችም በሞት አንነጠቅም ነበር" ስትልም ተናግራለች።
አዳዲስ ግኝቶች፤ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን እንደማይታመኑ እንዳሳዩዋትም ዚፖራ ገልጻለች።













