ቦይንግ 737 ማክስ የአውሮፕላን ምርቱን ለጊዜው ሊያቋርጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቦይንግ አምራች የሆነው ኩባንያ ለጊዜው የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርቱን ሊያቋርጥ መሆኑን አስታወቀ።
ላለፉት ዘጠኝ ወራት ባጋጠሙት ሁለት የመከስከስ አደጋዎች አውሮፕላኑ ከበረራ ታግዶ የነበረ ቢሆንም ማምረት ግን አላቋረጠም ነበር።
አውሮፕላኑ በኢትዮጵያና በኢንዶኔዢያ በገጠመው የመከስከስ አደጋ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
ቦይንግ አውሮፕላኑ ተመልሶ በዚህ ዓመት መጨረሻ እንዲበር አደርጋለሁ የሚል ተስፋ ሰንቆ ነበር።
የአሜሪካ አቪየሽን ተቆጣጣሪ ግን ይፋ እንዳደረገው አውሮፕላኑ እንዲህ በፍጥነት ተመልሶ አየር ላይ እንዲወጣ ፈቃድ እንደማይሰጠው አስታውቋል።
ሲያትል መቀመጫውን ያደረገው ቦይንግ፣ በአሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ምርቱን ወደ ውጪ የሚልክ ኩባንያ ነው።
ኩባንያው በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ከ737 ማክስ ጋር ተያይዞ ሰራተኞችን እንደማይቀንስ ገልጾ ነገር ግን ምርት ማቆሙ የእቃ አቅራቢ ድርጅቶችንም ሆነ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲል ተናግሯል።
የአውሮፕላኑ አምራች "737 ማክስ ደህንነቱ የተረጋገጠ ሆኖ ወደ በረራ እንዲመለስ ማድረግ ቅድሚያ ከምንሰጣቸው ተርታ ነው" ብሏል።
" 737 ማክስ ዳግም ወደ በረራ እንዲገባ ለማድረግ የሚሰጠው ፈቃድ፣ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎች፣ ጠንካራ መሆናቸውን እንዲሁም ተቆጣጣሪ አካላት፣ ደንበኞቻችን እና መንገደኞች ዳግም በ737 ማክስ ላይ ያላቸው እምነት መመለስ እንዳለበት እናምናለን" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው ሳምንት አሜሪካው የአቪየሽን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት አውሮፕላኑ በኢንዶኔዢያ ከተከሰከሰ በኋላ ተጨማሪ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ያውቅ እንደነበር ምክር ቤት ተገኝቶ ቃሉን ሰጥቷል።
የፌደራሉ አቪየሽን ባለስልጣናት አውሮፕላኑ ዲዛይኑ ላይ ለውጥ እስካልተደረገለት ድረስ በርካታ የአውሮፕላን አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ተናግረው እንደነበርም ያሳያል።
ይህ ሁሉ ሆኖ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን እስኪከሰከስ ድረስ አውሮፕላኑ ከበረራ አልታገደም ነበር።
ቦይንግ ለአውሮፕላኑ መከስከስ ምክንያት ነው የተባለውን የአውሮፕላኑን ስርዓት ዳግመኛ ዲዛይን እያደረገው ነው።
737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ በመታገዱ ብቻ 9 ቢሊየን ዶላር ያስወጣው ሲሆን የአክሲዮን ድርሻው በ4 በመቶ ቀንሶ ታይቷል።
ቦይንግ 400 737 ማክስ አውሮፕላኖችን አምርቶ ለደንበኞቹ ለማከፋፈል ተዘጋጅቶ ነበር።

















