ቦይንግ ለተጎጂ ቤተሰቦች መቶ ሚሊዮን ዶላር ሊሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢንዶኔዥያና ኢትዮጵያ ለተከሰከሱት ሁለት የ737 ማክስ አውሮፕላን ተጎጂ ቤተሰቦች ቦይንግ መቶ ሚሊዮን ዶላር አቀረበ።
ይህ ገንዘብ በሁለቱ አውሮፕላኖች አደጋ ለሞቱ በድምሩ ለ346 ተጎጂ ቤተሰቦች የሚሰጥ ነው።
ገንዘቡ የሟች ቤተሰቦችን የትምህርትና የኑሮ ወጪን የሚሸፍነው ነው ብሏል ቦይንግ።
ይህ ገንዘብ የሟች ቤተሰቦች በፍርድ ቤት ለከሰሱት ክስ የቀረበ ሳይሆን ድርጅቱ ከፍርድ ሂደቱ ውጭ ያደረገው ክፍያ ነው።
ቦይንግ ዛሬ ሰኔ 26፣ 2011 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ "የሚሰጠው ገንዘብ ለትምህርት፣ ከችግር ለመውጣት እንዲሁም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ለሆኑት ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት ኑሮና ለኢኮኖሚ ልማት ይውላል።
"ቦይንግ ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይተባበራል። ይሄ የመጀመሪያው ኢንቨስትመንትም በዓመታት ውስጥ የሚከፈል ይሆናል" ብሏል።
የቦይንግ ሊቀ መንበርና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴኒስ ሙይልንበርግ " ቦይንግ በሁለቱም አደጋዎች በተቀጠፈው ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ አዝኗል። የጠፋው ሕይወት በሚቀጥሉት ዓመታትም የሚረሳ አይሆንም" ሲሉ ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም "ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ላጡት ከልባችን ሀዘናችንን እየገለፅን ይሄ የመጀመሪያ ገንዘብ መፅናናትን ይፈጥርላቸዋል ብለን እናስባለን" ብለዋል።
በኢንዶኔዥያ ላየን ኤይርና በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጎጂ የሆኑት ቦይንግን የከሰሱት ሲሆን እስካሁንም ገና ውሳኔ ላይ አልተደረሰም።
ኩባንያው በኢንዶኔዥያ ላየር ኤይር አደጋ ለተጎዱት ጉዳዩን በስምምነት ለመጨረስና ብር ለመክፈል እየተነጋገረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጠቂዎችንም በስምምነት ለመፍታት ሀሳብ ቢያቀርብም በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡት ለመስማማት ዝግጁ እንዳልሆኑ አሳውቀዋል።












