ጊኒ ቢሳው ምርጫ፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምባሎ ፕሬዚደንት በመሆን ተመረጡ

ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኢምባሎ በጊኒ ቢሳው ያለውን የፖለቲካ ውጥረት ለመፍታት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል

የቀድሞው የጊኒ ቢሳው ጠቅላይ ሚኒስትር ኡማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ ተፎካካሪያቸውን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በማሸነፍ ፕሬዚደንት ሆነው ተመረጡ።

የ47 ዓመቱ ኢምባሎ ተቀናቃኛቸውን ዶሚንጎስ ሳይሞስ ፔሬራን 54 ለ46 በሆነ ድምፅ ማሸነፋቸውን የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ፔሬራ ግን የምርጫውን ውጤት "የተጭበረበረ ነው" ብለውታል።

ኢምባሎ ከአውሮፓዊያኑ 1974 ጀምሮ በተደጋጋሚ ዘጠኝ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች በታዩበት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ያለውን የፖለቲካ ውጥረት እልባት መስጠት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የቀድሞው ፕሬዚደንት ጆሴ ማሪዎ ቫዝ ባሳለፍነው በፈረንጆቹ ህዳር ወር በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ነበር ከውድድር ውጭ የሆኑት።

ጆሴ ሳይባረሩም ሆነ መፈንቅለ መንግሥት ሳይካሄድባቸው የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ የአገሪቷ መሪ ይሁኑ እንጅ፤ ፖለቲካዊ ቀውሶችን ችላ በማለትና እንደተስፋፋ የሚነገረው ሙስና ስማቸውን አጥልቶታል።

የምርጫ ዘመቻ ቡድኑ ተቀናቃኛቸውን በምርጫ መጭበርበር ከስሰዋል። ነገር ግን የምዕራብ አፍሪካ ኢኮዋስ ክሱን አለመቀበሉን ገልፆ፤ የአገሪቷ የጦር ኃይል ሥርዓት ለማስከበር በተጠንቀቅ ላይ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የምርጫ ታዛቢዎች በበኩላቸው ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው ምርጫ ላይ የድምፅ ማጭበርበርን የሚያመላክት ምንም ማስረጃ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ይሁን እንጅ ገዥ ፓርቲ የነበረው ፔ ኤ አይ ጂ ሲ መሪ የነበሩት ፔሬይራ፤ የምርጫው ውጤት፤ "ያልተመጣጠነ፣ ጥሰት የታየበት ነው" ብለውታል። ጉዳዩንም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚያደርሱት ዝተዋል።

በቅፅል ስማቸው 'ጀኔራሉ' በመባል የሚታወቁት የተቃዋሚ ተመራጭ እና የቀድሞ የአገሪቷ የጦር አዛዥ የነበሩት ኢምባሎ ከአውሮፓዊያኑ 2016 አስከ 2018 ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

ፕሬዚደንቱ የአገሪቷን አንድነት ለማስጠበቅ፣ የ1.6 ሚሊየን ሕዝቦች መኖሪያ የሆነችውንና ከዓለም አገራት በድህነት የምትታወቀውን አገራቸውን ለማዘመን እና ድህነትን ለመቀነስ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን የአደንዛዥ እፅ ዝውውር፣ ድህነትና ያልተረጋጋው የአገሪቷ ፖለቲካዊ ሁኔታ ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል ተብሏል።