የኢትዮጵያዊው ጉዞ፡ ከኬኒያ የስደተኞች ካምፕ እስከ ሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ

ኤልሻዳይ እና ቤተሰቦቹ

የፎቶው ባለመብት, ኤልሻዳይ ጌትነት

የምስሉ መግለጫ, ኤልሻዳይ እና ቤተሰቦቹ

ኤልሻዳይ ጌትነት ይባላል፤ በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ቀዶ ጥገና የዶክትሬት ተማሪ ነው። ኤልሻዳይ ከስደተኞች ካምፕ ተነስቶ እስከ ካናዳ ያደረገውን ጉዞ አካፍሎናል።

አባቱ በደርግ ዘመን የነበረውን ወታደራዊ ግዴታ ካጠናቀቁ በኋላ ከእናቱ ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ ለቀው ለመውጣት ተስማሙ። አገራቸውን ለቀው ወደ ኬንያ ለመሰደድ ሲያቅዱ ሁለቱም በአሥራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ ነበር የሚገኙት።

''እንደውም እናቴ እንደነገረችኝ ለሴት አያቴ ቡና ከምታፈላበት ድንገት ተነስታ 'መጣሁ' ብላ እንደወጣች ነው ኬንያ የገባችው። ከዛም ከአባቴ ጋር ተያይዘው ጉዞ ወደ ኬንያ ጀመሩ።''

በእግር እና በመኪና የተደረገው ጉዟቸው እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነበር። ጫካዎችን በሚያቋርጡበት ወቅት አንዳንዶቹ ስደተኞች በአንበሳ እንደተበሉም ወላጆቹ የነገሩትን ኤልሻዳይ ያስታውሳል።

ቤተሰቦቹ ከአዲስ አበባ ተነስተው የኬንያ ድንበር ለመድረስ 23 ቀናት የፈጀባቸው ሲሆን፤ በመጀመሪያ መርሰቢት የሚባለው የስደተኞች ማቆያ ውስጥ ነበር የገቡት። የደርግ ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ቢነገራቸውም 'አንዴ ወጥተናል አንመለስም' ብለው ሌላ አማራጭ መፈለግ ያዙ።

አንድ ከብቶቹን ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ የሚወስድ ገበሬ አግኝተው፣ እነሱንም ይዟቸው እንዲሄድና በምላሹ ገንዘብ ሊከፍሉት ተስማሙ። በመጨረሻም ከከብቶች ጋር መኪና ውስጥ ተጭነው በድብቅ ናይሮቢ ገቡ።

ናይሮቢ ከደረሱ በኋላም በኬንያና ሶማሊያ ድንበር ላይ ወደሚገኝ ዳዳብ ወደተባለ የስደተኞች ማቆያ ተዘዋወሩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ኤልሻዳይ በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ተወለደ።

ኤልሻዳይ እና አባቱ አቶ ጌትነት

የፎቶው ባለመብት, Elshadai Getenet

የምስሉ መግለጫ, ኤልሻዳይ እና አባቱ አቶ ጌትነት

"እናቴ ኤልሻዳይ የሚለውን ስም የሰጠችኝ በምክንያት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤልሻዳይ ማለት ሁሉን ቻይ ማለት ነው። እኔ የተወለድኩት በስደተኞች ማቆያ ውስጥ ሲሆን፤ እዛ የተወለዱ ብዙ ህጻናት በወባና በምግብ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸው ያልፍ ነበር። እናቴ በምንም አይነት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ብትሆን ፈጣሪ እንደሚጠብቀኝ ተስፋ ታደርግ ነበር። ለዚህም ነው ይህንን ስም የሰጠችኝ።"

ምንም እንኳን በዛ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ልጆችን ማሳደግ ከባድ ቢሆንም፤ በአካባቢው የነበሩ ሌሎች ስደተኞችም ጭምር ተባብረው ልጆችን ያሳድጉ እንደነበር ኤልሻዳይ ያስታውሳል።

''እኛ የነበርንበት የስደተኞች ማቆያ በብዛት ሶማሌዎች የሚገኙበት ነበር። የባህል እንዲሁም የሃይማኖት ልዩነት ቢኖርም ያለምንም ችግር ነበር ያደግኩት። ሁሉም ሰው ይንከባከበኝ ነበር።''

አፉን በአማርኛ የፈታው ኤልሻዳይ፤ አራት ዓመት ሲሞላው ሶማልኛ እና ስዋሂሊ በተጨማሪነት አቀላጥፎ መናገር ይችል ነበር።

''በነበረው አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ምክንያት እናቴ የራሷን ልብሶች እየቀደደች ለኔ ልብስ ትሰፋልኝ ነበር። አባቴም ቢሆን በዛ በረሃ ውስጥ ጫማ እንኳ ሳያደርግ የጉልበት ሥራ እየሠራ ለእኔ ጫማ ይገዛልኝ ነበር። በወር የሚሰጠን ቀለብም እጅጉን ትንሽ ነበር። ለአንድ ቤተሰብ በወር 2 ኪሎ ምግብ ብቻ ነበር የሚሰጠው። ነገር ግን ስደተኞቹ ተሰባስበው ህጻናቱ እንዳንራብ ይጥሩ ነበር" ሲል ያስታውሳል።

የካምፑ ነዋሪዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ቢገጥማቸውም፤ ሁሌም ቢሆን አዋቂዎች በቅድሚያ ለህጻናት ምግብ ይሰጡ ነበር ይላል ኤልሻዳይ።

''ሌላው ቀርቶ የወለዱ እናቶች የሌላ ሰው ልጆችን ጭምር ያጠቡ ነበር።''

በስደተኞች ማቆያው ውስጥ መኖሪያ ቤት ማግኝት ከባድ እንደነበርም ያስታውሳል። "እኔና ቤተሰቦቼ የምንኖረው በትንሽዬ ጎጆ ውስጥ ነበር። አባቴ ወታደር ስለነበር ጠንካራ እንድሆንና በቀላሉ እጅ እንዳልሰጥ አድርጎ አሳድጎኛል'' ይላል።

የኤልሻዳይ አባት የኢትዮጵያን ጀግኖች ታሪክ ይተርኩለት እንደነበርም ይናገራል።

''ሁሌም ቢሆን ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ታሪክ ይነግረኝ ነበር። ስለ አፄ ቴዎድሮስ፣ ጉንደት ላይ የግብፅን ጦር ስላሸነፈው አፄ ዮሃንስ፣ ሙሉ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ቅን ገዢ ጣልያኖችን ከኢትዮጵያ ስላባረረው አፄ ምኒሊክ እንዲሁም በዲፕሎማሲ ሥራቸው ስለሚታወቁት አፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ እየሰማሁ ነው ያደግኩት። በተጨማሪም እንደ ባልቻ ሳፎ፣ ራሥ ጎበና፣ ንግሥት ጣይቱና ሌሎችም ጀግኖች ሕይወትና አኗኗር መስማት በልጅነቴ ትልቅ ቦታ ነበራቸው።"

የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ብዙ ህጻናት ስላልነበሩ ከሌሎች ህጻናት ጋር ተቀላቅሎ የማደግ እድልን አላገኘም ነበር ኤልሻዳይ።

የኤልሻዳይና ወላጆቹ በተለያዩ ጊዜያት

የፎቶው ባለመብት, Elshadai Getenet

የምስሉ መግለጫ, የኤልሻዳይና የወላጆቹ የህይወት ጉዞ

ጉዞ ወደ ካናዳ

''በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ለአምስት ዓመታት ከቆየን በኋላ ወደ ካናዳ የምንሄድበት እድል ተፈጠረ። ሕይወታችንም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀየረ። በመጀመሪያ በኖቫ ስኮሺያ ግዛት ሃሊፋክስ ከተማ ለአንድ ዓመት ቆየን።''

''በመቀጠል ደግሞ ካልጋሪ ወደምትባል ከተማ ተዘዋውረን አዲስ ሕይወት መሰረትን። ልክ እንደማንኛውም ስደተኛ ከፍተኛ የሆነ የባህል መጣረስ ቢያጋጥመንም ቀስ በቀስ በራስ መተማመናችን እየጨመረና እየተላመድነው መጣን።''

ኤልሻዳይ የትምህርት ውጤቱ በጣም ጥሩ ስለነበር የካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ዲግሪ ፕሮግራም ተቀበለው። በሰዓቱ ምን አይነት ዘርፍ ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ እርግጠኛ ባይሆንም በጤናው አካባቢ ግን ፍላጎት እንዳለው ያውቅ ነበር።

ከዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው በአንዱ ቀን፤ ወደተለያዩ አገራት በመጓዝ ነጻ የጥርስ ህክምና ይሰጥ የነበረ ዶክተር ራልፍ ዱቤኒስኪ የሚባል ግለሰብ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያና ሩዋንዳ እንደሚጓዝ ነግሮት አብሮት እንዲሄድ ጥያቄ አቀረበለት።

ኤልሻዳይ አይኑን ሳያሽ ነበር ሃሳቡን የተቀበለው።

"እ.አ.አ. በ 2012 ከዶክተር ራፍ ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ አገሬን በአይኔ ለመመልከት በቃሁ። አዲስ አበባንና ቤተሰቦቼ ያደጉበት ልደታ ሰፈርንም ለማየት እድሉን አገኘሁ። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ስሄድ የመጀመሪያዬ ቢሆንም ልክ ስደርስ ቤቴ የተመለስኩ አይነት ስሜት ነበር ተሰማኝ'' ሲል ወቅቱን ያስታውሳል።

ዶክተር ራልፍና ኤልሻዳይ ከወሊሶ ወጣ ብላ ወደምትገኝ ሃርቡ ጩሉሌ ወደምትባል ትንሽ መንደር ተጉዘውም ነበር። በነበራቸው ቆይታ ወላጅ አልባ ለሆኑ ህጻናት ቤት ሲገነቡ፣ የጥርስ ህመም ለነበረባቸው ሰዎች ህክምና ሲሰጡና ቀላል ቀዶ ጥገና ሲያደርጉ እንደቆዩ ይናገራል።

''እሱ የህክምና ሥራዎቹን ሲሠራ አብሬው እየሄድኩ አግዘው ስለነበር የአካባቢው ልጆች እኔም የህክምና ባለሙያ መስያቸው 'ዶክተር' እያሉ ይጠሩኝ ነበር። በዚህ ሁኔታ በጣም ነበር የተገረምኩት። የአገራቸው ሰው ህክምና ላይ ተሰማርቶ በመመልከታቸው በጣም ተደስተው ህጻናት ሲያደንቁኝ ማየት ተጨማሪ መነሳሳትና ጉጉትን ፈጥሮብኝ ነበር።"

''ጉዞዬን ጨርሼ ወደ ካናዳ ስመለስ በአገሬ ባህልና ታሪክ በእጅጉ ተነክቼና አዲስ ሰው ሆኜ ነበር የተመለስኩት። የቀደሙት አባቶቼ እንደ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደሩ ቤተ መንግሥትና አክሱም ሀውልት ያሉ ቅርሶችን በራሳቸው መገንባት ከቻሉ፤ እኔም ምንም አያቅተኝም የሚል ስሜት አደረብኝ።''

ኤልሻዳይ ጌትነት

የፎቶው ባለመብት, Elshadai Getenet

የምስሉ መግለጫ, ኤልሻዳይ ጌትነት

ኤልሻዳይ በካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ሁለት ወይም ሦስት ተጨማሪ ሥራዎች ይሠራ ነበር። ''ቀላል አልነበረም ግን መድረስ የምፈልግበትን ቦታ አውቅ ስለነበር ያለምንም ችግር ተወጥቼዋለው'' ይላል።

የመጨረሻው ዓመት ላይ በጥርስ ቀዶ ህክምና በእጅጉ በሚታወቀው የአውስትራሊያው ሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ ለተጨማሪ ትምህርት አመለክቶ ነበር። እ.አ.አ. በ2018 መጨረሻ አካባቢ ደግሞ ከሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ ሙሉ በሙሉ እንደተቀበሉት የሚገልጽ ኢሜይል ደረሰው።

''እውነቱን ለመናገር በሕይወቴ እጅግ በጣም አስደሳቹ ቀን ነበር ማለት እችላለሁ። አስታውሳለሁ መልዕክቱ ሲደርሰኝ ማልቀስ ጀመርኩ፤ ቤተሰቦቼም ምን ሆነ ብለው ተደናግጠው ነበር። ምናልባት የቤተሰብ አባል ወይም ከጓደኞቼ መካከል አንዳቸው መጥፎ ነገር ያገጠማቸው ነበር የመሰላቸው።''

''ልክ የኢሜይል መልእክቱን ሳሳያቸው እናቴ 'እግዚአብሔር ይመስገን' ብላ መሬት ላይ ወደቀች። በተደጋጋሚ 'እግዚአብሔር ይመስገን' ትል ነበር። አባቴ ደግሞ በቆመበት ከአይኖቹ እንባ እየወረደ እንደነበር አስታውሳለው። ሦስታችንም ተቃቅፈን ቆየን።''

''ለቤተሰቦቼ በጣም ትልቅ አጋጣሚ ነበር፤ ምንያቱም ከስደተኞች ካምፕ እስከ ካናዳ ያደረጉትን የመከራ ጉዞ የሚያስረሳ ስለሆነ ነው። ልፋታቸው ሁሉ መና ባለመቅረቱ እነሱም እኔም በጣም ደስተኞች ነን።"

በአሁኑ ወቅት በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱን ሊያጠናቅቅ እንደተቃረበ የሚናገረው ኤልሻዳይ፤ በእያንዳንዱ ቀን ከባድና አስቸጋሪ ፈተናዎችን ማለፍ ግድ እንደሆነ ያስረዳል ሆኖም ግን "ከአቅሜ በላይ የሚሆን ነገር የለውም። ማንኛውንም አይነት ፈተና ለማለፍ ዝግጁ ነኝ" ይላል።

"በትምህርት ክፍሉ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሆኔ ደግሞ አገሬን በአግባቡ እንድወክልና ጠንክሬ እንድሠራ አድርጎኛል።"

ኤልሻዳይ አንዳንዴ ለትምህርት ወደ ክፍል ሲገባ ጋቢ ይለብሳል። የክፍል ጓደኞቹና አስተማሪዎቹም በጣም እንደወደዱትና ሁሉም 'ጋቢ እንፈልጋለን' እንዳሉትም ይናገራል። ክሊኒክ ውስጥ ሲሆን ደግሞ ገዋኑ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ያደርዳል።

"ለአሁኑም ለወደፊቱም ለስኬቴ ትልቁን ሚና የሚጫወተው የቤተሰቦቼ ያልተቋረጠ ድጋፍና ሁሌም ከጎኔ የሆኑ ሰዎች አበርክቶ ነው። የአገሬን ታሪክና ባህል ማወቄም እራሴን በደንብ እንዳውቅና ስኬታማ እንደሆን እንደረዳኝ አስባለው" ሲል ይገልጻል።

ኤልሻዳይ ጌትነት ነጠላ ለብሶ የትምህርት ክፍል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Elshadai Getenet

የምስሉ መግለጫ, ኤልሻዳይ ነጠላ ለብሶ

ኤልሻዳይ እንደሚለው፤ አስቸጋሪና ተስፋ አስቆራጭ ነገር ሲያጋጥመው፤ ወራሪ ኃይልን ለመዋጋትና አገራቸውን ከጠላት ለመከላከል ወደ አድዋ ስለዘመቱት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ያስባል።

"እነሱ ተስፋ ቆርጠው ቢሆን ኖሮ የምናውቃት ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር። እነሱ በዛ አስቸጋሪ ሁኔታ ተስፋ ሳይቆርጡ እኔ እንዴት ተስፋ እቆርጣለሁ?"

"የአሁኑ የኢትዮጵያውያን ጦርነት አድዋ ላይ አይደለም። ጦርነቱ በትምህርት ቦታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በሕግ እና በመሳሰሉ ዘርፎች ነው። በመላው ዓለም ብዙ ዳያስፖራዎች አሉ፤ ይህንን እንደ ትልቅ እድል ልናየውና ልንጠቀምበት ይገባል።"

"ምናልባት የኔ ቤተሰቦች ከአገር በመውጣታቸው ይህንን ዕድል አግኝቼ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ስደት የሁሉም ነገር መፍትሄ ነው ብዬ አላስብም። ሁላችንም ከተባበርን ይቺን አገር ወደ ተሻለ ቦታ ማድረስ የምንችል ይመስለኛል። እኔ ባለኝ እውቀትና ልምድ የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግና ሌሎችን ለተሻለ ነገር ለማነሳሳት ዝግጁ ነኝ።"

ኤልሻዳይ "የቀድሞ አባትና እናቶቻችን ያኖሩልንን ገናና ታሪክና ባህል ወደ ቀድሞው ታላቅነቱ ለመመለስ ሁላችንም እንሥራ" ሲልም ይናገራል።