ስዊዲን፡ ስለ ሀብት ማውራት ነውር የሆነባት አገር

በስዊድኗ መዲና ስቶክሆልም ባለጸጎች በሚኖሩበት ኦስተርማልም፤ በግል መርከባቸው የሚንሸራሸሩ ሰዎችን ማየት ብዙ አያስገርምም። ከዚህ አካባቢ ብዙም የማይርቀው ስትራንድቫገን በቅንጡ መኖሪያ ህንጻዎች የተሞላ ነው።
እጅግ ውድ የኮስሞቲክስ ሱቆች፣ ጥቂቶች ብቻ የሚስተናገዱባቸው ሬስቶራንቶች ያሉበት አካባቢ ቢሆንም እንኳን፤ ስለ ሀብት ንብረቱ በዝርዝር ለማውራት ፍቃደኛ የሆነ ሰው ማግኘት ግን ቀላል አይደለም።
የ30 ዓመቱ ሮበርት ኢንገማርሰን፤ ገንዘቡን ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስደስተው ገልጾ፤ "ምን ያህል ገንዘብ እንደማገኝ የምናገርበት ምክንያት ስለማይታየኝ አላወራም" ይላል።
የ24 ዓመቱ ቪክተር ሄስ፤ ስዊድን ውስጥ ታዋቂ በሆነ ድርጅት ውስጥ ሊቀጠር መሆኑን ቢናገርም ደሞዙን ሲጠየቅ፤ "እሱማ ሚስጥር ነው" ሲል መልስ ሰጥቷል።
ከጎርጎሮሳውያኑ 1990 ወዲህ በስዊድናዊያን ሀብታሞችና ድሆች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል። ከሕዝቡ 20 በመቶው ከተቀረው ማኅበረሰብ አራት እጥፍ ገቢ ያገኛል።
በብዙ አገራት መለኪያ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ስኬታማ ከሚያስብሉ መስፈርቶች አንዱ ነው። በስዊድናውያን ዘንድ ግን ስለ ሀብትና ንብረት ማውራት ነውር ነው።
ቢቢሲ ይህንን ዘገባ ሲያጠናቅር ከወጣት ባለሀብቶች ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ በተደጋጋሚ ቢሞክርም ውጤታማ አልሆነም። ባለጸጎቹ ስለ ቄንጠኛ ቤታቸው፣ ውድ መኪናቸው ኢ-መደበኛ በሆነ ንግግር መካከል ቢያወሩም፤ አደባባይ ወጥተው ሀብቴን እወቁልኝ ለማለት አይፈቅዱም።
"ስለሀብቴ ማውራት ጉራ መንዛት እንደሆነ ይሰማኛል፤ ያን ማድረግ ደግሞ ምቾት አይሰጠኝም" ሲል አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ገልጿል።
ስቶክሆልም ውስጥ ስለሀብት ማውራት ለምን አስነዋሪ ሆነ?
ስቶክሆልም ውስጥ ከአስር ዓመታት በላይ የኖረችው ሎላ አኪንማዴ አከርስቶርም፤ ስለ ስዊድን ባህል መጽሐፍ አሳትማለች። ስዊድን ውስጥ ስለ ሀብት ማውራት "ምቾት አይሰጥም" ትላለች።
ይህን ያህል ገንዘብ አለኝ ብሎ መኩራራት ወይም ስለ ወርሃዊ ደመወዝ ማውራትም ነውር እንደሆነ፤ "ስዊድናዊያን ስለ ገንዘብ ከማውራት ይልቅ ስለ ወሲብ ማውራት ይቀላቸዋል" ስትል ታስረዳለች።
ለዓመታት አሜሪካ የኖረችው የ28 ዓመቷ ስዊድናዊት ጋዜጠኛ ስቲና ዳልግረን ተመሳሳይ አስተያየት ትሰነዝራለች።
"አሜሪካ ውስጥ ይህን ያህል ገንዘብ አገኛለሁ ብትይ፤ ሰው ሁሉ ያሞግስሻል፤ 'ጎበዝ! በርቺ!' ይልሻል። ስዊድን ውስጥ የደመወዝሽን መጠን ብትናገሪ ግን ሰው 'ጤና የላትም እንዴ?' ብሎ በመገረም ያይሻል። ስዊድን ውስጥ ስለ ደመወዝ፣ ስለ ገንዘብ አይጠየቅም።"
ስዊድን ውስጥ ስለ ገንዘብ ማውራት አስነዋሪ ባህል መሆኑን የሚገልጸው ቃል 'ጃንተላግን' ይባላል። ይህ ባህል አንድ ሰው ከማንም በላይ ነኝ ብሎ ማሰብ እንደሌለበት ያስገነዝባል።
ጸሐፊዋ ሎላ እንደምትለው ይህ ያልተጻፈ ማኅበራዊ ሕግ፤ አንድ ሰው 'እዩኝ እዩኝ' እንዳይል፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እኩልነት እንዲሰፍን ያደርጋል።
'ጃንተላግን' የሚለው ቃል የተወረሰው በ1933 አክሰል ሳንደሞስ በተባለ ደራሲ ከተጻፈ ልብ ወለድ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ከሕግ ዝንፍ ማለት የማይቻልባት 'ጃንቴ' የምትባል ከተማ አለች። ባህሉ ከመጽሐፉ የተወሰደ ነው ቢባልም፤ ዶ/ር ስቴፈን ትሮተር የተባሉ ምሁር፤ ባህሉ ለዘመናት በኖርዲክ አገራት በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች እንደነበረ ይገልጻሉ።
"ማኅበረሰቡን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ነው፤ ስለ ሀብት አለማውራት ብቻ ሳይሆን የማያውቁትን ነገረ አለመዘባረቅንም ያካትታል።"
ሎላ በበኩሏ፤ ስዊድን 'መደብ አልባ አገር ናት' የሚል ገጽታ ለመገንባት ቢሞከርም፤ ሀብታም ሰዎች ጓደኛ የሚያደርጉት ባለጸጎችን ነው። ሲሰባሰቡም ስላላቸው ገንዘብ ያለገደብ ያወራሉ። ስለዚህም የ'ጃንተላግን' ሕግ አንጻራዊ ነው ትላለች።
ወጣት ስዊድናዊያን እና 'ጃንተላግን'
ወጣት ስዊድናዊያን 'ጃንተላግን'ን መተቸት ጀምረዋል። ስለ ሀብትና ውጤታማነት በግልጽ መወራት እንዳለበትም ያምናሉ።
የ22 ዓመቷ ጦማሪ ኒኮል ፋልሲያኒ የብዙ ወጣቶችን አመለካከት ትወክላለች። ሀብታሟ ጦማሪ ለሠርጓ የ20 ሺህ ዶላር ሻምፓኝ እንደተጠጣ የተናገረችው ያለምንም መሸማቀቅ ነበር።
"ይህ ሀብትን የመደበቅ ባህል ቢጠፋ ደስ ይለኛል፤ ሁሉም ሰው እኩል ነው የሚለው አስተሳሰብ መልካም ቢሆንም፤ ጥሮ ግሮ ሀብት ያካበተ ሰው መኩራራት አለበት።"
በኖርዌይ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ኮርንሊዩስ ካፕሊን፤ የአመለካከት ለውጥ ለመምጣቱ ምክንያት የሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ ገናናነት ነው ይላሉ።
ወጣቶች ከእድሜ እኩዮቻቸው በተለየ ነጥረው ለመውጣት ስለእራሳቸው ጥሩ የሆነን ነገር ባጠቃላይ ያወራሉ። እንዲያውም 'ጃንተላግን' እንደ ስድብ እየተቆጠረም መጥቷል።
ሎላ እንደምትለው፤ ወጣቶች ስኬታቸውን በአደባባይ ለማውራት አይፈሩም። ከተለያዩ አገሮች ወደ ስዊድን የሚያቀኑ ስደተኞች ቁጥር መጨመርም 'ጃንተላግን' እየጠፋ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህም፤ ሎላ ስለ ገንዘብ ማውራት አስነዋሪ መሆኑ እየተሸረሸረ እንደሚሄድም ታምናለች።
በተቃራኒው አንዳንድ ስደተኞች 'ጃንተላግን'ን መውረሳቸውን ይናገራሉ። ከሦስት ዓመታት በፊት ስቶክሆልም መኖር የጀመረችው የ35 ዓመቷ የቺሊ ተወላጅ ናታሊያ ኢርቢራ አንዷ ናት።
"ቺሊ ውስጥ ጎበዝ ተማሪ ቆንጆ፣ ባለ መኪናና ባለቤት መሆንም ያኩራራል። እዚህ አገር ግን ሰዎች ስለስኬታቸው አይወሩም፤ በእኔ እምነት ራስን አለመካብ የሚበረታታ ባህሪ ነው።"












