ግዙፍ መፈንቅለ መንግሥትን የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች በሱዳን ውስጥ ተካሄዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሱዳን የተካሄደው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሦስተኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ጦር ሠራዊቱ ሥልጣን መቆጣጠሩን የመቃወሙ በርካታ ሕዝብ የተሳተፈባቸው የተቃውሞ ሰልፎች በመላው ሱዳን ተካሄዱ።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተሳተፉበትና በዋና ከተማዋ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጋዝ መተኮሳቸው ተነግሯል።
ሦስተኛ ዓመቱ እየታሰበ ያለው ሕዝባዊ ተቃወሞ ሱዳንን ለሰላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአምባገነንነት የመሩትን ኦማር ሐሰን አልበሽርን ከሥልጣን እንዲወገዱ አድርጓል።
ይህንንም ተከትሎ የሽግግር መንግሥት የመሰረቱት የሱዳን ሲቪል ፖለቲከኞችና የጦር ሠራዊት ጀነራሎች ባለፉት ዓመታት በሥልጣን ክፍፍል ላይ ሳይግባቡ ቆይተው ባለፈው ጥቅምት ወር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ ይታወሳል።
የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ጄነራል አል ቡርሐን ያካሄዱት መፈንቅለ መንግሥት ከሱዳናውያንና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከባድ ተቃውሞ ስለገጠመው፣ በቁም አስር ላይ የቆዩትን ሲቪሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ተገዷል።
ነገር ግን ይህ ተቃውሞውን ለማርገብ የጦር ሠራዊቱ የወሰደው እርምጃ በሱዳን ውስጥ የሚካሄደውን ተቃውሞ አላስቆመውም።
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ አሁንም የሚጠይቁት ወታደሮች ከአገሪቱ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ወጥተው አመራሩ ሙሉ ለሙሉ በሲቪል ፖለቲከኞች እንዲያዝ ነው።
እሁድ ዕለት ካርቱም ውስጥ በተደረገው ሰልፍ ተቃዋሚዎች የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የሆኑት የጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን መቀመጫ ወደሆነው ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅንተው ነበር።
ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ "ሕዝቡ ጠንካራ ነው፣ ማፈግፈግ የለም" እና ጄነራል ቡርሐን ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቁ መፈክሮችን አሰምተዋል።
"ሐምዶክ ወደ ሥልጣን ቢመለሱም የትኛውም አይነት መፈንቅለ መንግሥትን አንቀበልም። ያካሄድነው አብዮት ሙሉ የሲቪል ተቋማትና ሥልጣን እንዲኖር እንጂ ለግለሰቦች አይደለም" ሲል አንድ የተቃውሞ ሰልፈኛ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግሯል።
የተቃውሞ ሰልፎች ከዋና ከተማዋ ካርቱም ባሻገር በሌሎች በርካታ ከተሞች ተካሂደዋል።
ሰልፎቹን በተመለከተ የወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት ተቃዋሚዎች የአገሪቱን ሰንደቅ አላማና በሕዝባዊ አመጹ ወቅትና ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ምስሎች ይዘዋል።
አንድ የዶክተሮች ቡድን ባወጣው መረጃ ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ቢያንስ 45 ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል።
ከሦስት ዓመት በፊት በተደረሰውና ባልተከበረው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት መሠረት የሱዳን የሽግግር መንግሥት መሪ የነበሩትና የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አል ቡርሐን ሥልጣናቸውን ለሲቪል ፖለቲከኞች ማስረከብ የነበረባቸው ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ነበር።
ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰዎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ እያነሳሱ በመሆናቸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል ነው ሲሉ የእርምጃቸውን ተገቢነት ገልጸው ነበር።
ጄነራሉ እንደሚሉት ሱዳን አሁንም በሽግግር ሂደት ላይ እንደሆነችና አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሻገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ወደ ሥልጣናቸው ከተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በተደረሰው ስምምነት ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የባለሙያዎች ካቢኔ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
ነገር ግን አዲሱ የሲቪል መንግሥት በጦር ሠራዊት ጀነራሎች የበላይተቆጣጣሪነት ስር ስለሚሆን አገሪቱን በሚመራበት ጊዜ የሚኖረው ሥልጣን ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ለወራት ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም በሱዳን ጎዳናዎች ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሱዳናውያን ግን በጦር ኃይሉ ላይ እምነት ስለሌላቸው የትኛውም አይነት የሥልጣን መጋራት ስምምነትን ፈጽሞ አይቀበሉትም።
"ለሰልፍ የወጣሁት የተደረሰው ፖለቲካዊ ስምምነት ሕዝቡን የሚወክል ስላልሆነ ሙሉ ለሙሉ ለመቃወም ነው" ሲል አንድ ካርቱም ውስጥ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈ ግለሰብ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, AFP














