የሱዳን ጦር የተባበሩት መንግሥታትን ድጋፍ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የተባበሩት መንግሥታት የሽግግር መንግሥቱን እንዲደግፍ ጥሪ አቀረቡ።
ጀነራል አል-ቡርሃን ይህን ጥያቄ ያቀረቡት የተመድ የሱዳን ተወካይ የሆኑትን ቮልከር ፔርዝስ አግኝተው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
የተመድ ተወካዮ ከአል-ቡርሃን ጋር መገናኘታቸውን በትዊተር ገጻቸው የገለጹ ሲሆን፤ ምንም አንኳ ሱዳን ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት እንዲመለስ ብትስማም፤ ሌሎች ቁልፍ የሆኑ ጉዳዮች መከናወን አለባቸው ብለዋል።
ጀነራል አል-ቡርሃን ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ከተደረጉት የሲቪል መንግሥት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር አብሮ ለመሥራት እና ምርጫ እስኪከናወን ድረስ አብደላ ሐምዶክ ለሚመሰርቱት የሽግግር መንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የሱዳን ጦር በጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራውን የቪሲል መንግሥት ገልብጦ ሥልጣን ተቆጣጥሮ እንደነበረ ይታወሳል።
በቁም እስር ላይ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ከቀናት በፊት ከሱዳን ጦር ጋር ከስምምነት ደርሰው ወደ ሥልጣናቸው ተመልሰዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት አብደላ ሐምዶክን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የሾመው የሲቪል ፖለቲከኞች ስብስብ ግን ከወታደሮች ጋር የሚደረግን ማንኛውንም አይነት አዲስ ስምምነት አልቀበልም ሲል ነበር።
ይሁን እንጂ በሱዳን የመንግሥት ግልበጣ ማግስት የጀመሩት የተቃውሞ ሰልፎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ድምጻቸውን በአደባባይ ለማሰማት የሚወጡ ሰዎች በሱዳን ጦር መሪዎች ላይ ያላቸው ተቃውሞ እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጹ ቆይተዋል።
በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ የሲቪል አስተዳደሩን አመራሮች ከበተነና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ መፈንቅለ መንግሥቱን ተቃውመው አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል ቢያንስ 40 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ የአገሪቱ ዜጎች ሱዳን ወደ ሰላማዊ የዲሞክራሲ ሽግግር እንድትመለስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት በ18 ወራት ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂድ ጫና እየተደረገበት ነው።












